ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በዘንድሮው ክረምት፣ በተለይም እሰከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ የጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ የተነሳ 170 ሺኅ ነዋሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተሰማ።
በጎርፉ 130 ሺኅ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመነ ዳሮታ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የነበረውን ልምድ ከግንዛቤ በማስገባት፣ በዚህ ዓመት ክረምት ወቅት በጎርፍ ምክንያት ወደ 2 ሚሊየን ያህል ሰዎች ሊጎዱ፣ 434 ሺኅ ያህሉ ደግሞ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብሎ ግምት ተይዞ ነበር።
እስካሁን ድረስ በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ በአፋር ክልል የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ወደ 67 ሺኅ 885 አካባቢ ሲሆን፣ 40 ሺኅ 130 አካባቢ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
ደቡብ ኦሞ ዳሰነች አካባቢ በኦሞ ወንዝ ሙላትና የግቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ ውሃ በተወሰነ መልኩ መልቀቁን ተከትሎ በደረሰ የጎርፍ አደጋ በኦሞ በሚገኙ ከ15 ሺኅ በላይ ሰዎች እንዳይጎዱ ከሚኖሩበት አካባቢ የማውጣት ሥራ እንደተከናወነ ተሰምቷል።
ተፈናቃዮቹ በጊዜያዊ መጠለያ እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን፣ ከ10ሺኅ በላይ ለሚሆኑት የተለያዩ ድጋፎች እንደደረሰና ለቀሪዎቹ 5 ሺኅ ሰዎች ደግሞ ድጋፍ ለማድረስ እየተሠራ እንደሚገኝ ከኮሚሽነሩ መግለጫ መረዳት ተችሏል።
በያዝነው ዓመት በልግ ወቅት በደረሰው የጎርፍ አደጋ ምክንያት 470 ሺኅ ያህል ነዋሪዎች ጉዳት ሲደርስባቸው ከ300 ሺኅ በላይ የሚሆኑት መፈናቀላቸውን ያመላከተው መግለጫ፤ ይህን የበልግ ወቅት አደጋን ለመቋቋም ሥራ እየተሠራ ባለበት ወቅት፣ የክረምቱ ዝናብ ከበልጉ ዝናብ ጋር ተያይዞ በመምጣቱ ወንዞችና ግድቦች ስለሞሉ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።