የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ28 ዓመት በኋላ በአ/አ ገርጂ አካባቢ 510 ቤቶችን ግንባታ...

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ28 ዓመት በኋላ በአ/አ ገርጂ አካባቢ 510 ቤቶችን ግንባታ ጀመረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና  ላለፉት 28 ዓመታት አቋርጦት የነበረውን የቤቶች ግንባታ 3 ቢሊየን ብር ወጪ በአዲስ አበባ ሊጀምር መሆኑን የፌደራል ቤቶች ግንባታ ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

አዲስና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም ኮርፖሬሽኑ በገርጂ ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ መንደር ውስጥ 510 ቤቶችን በ3 ሄክታር ይዞታ ላይ ለመገንባት ኩምጋንግ እና ኦቪድ ከተባሉ የግንባታ ተቋራጮች ጋር የውል ስምምነት መፈራረሙን ዛሬ ይፋ ሆኗል።
የሚታየውን የመንግሥት ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ 3 ቢሊየን ብር ወጪ በማድረግ በአጭር ጊዜ፣ በአነስተኛ ዋጋ እና በአዲስ ቴክኖሎጂ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት ሥራ እንደተጀመረ የገለጹት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ረሻድ ከማል፤ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞችበሚገጥማቸው የመኖሪያ ቤት እጥረት ምክንያት ሥራቸውን በትኩረት ለመሥራት እንደሚቸገሩ ጠቁመው፣ ይህ ፕሮጀክት በተወሰነ ደረጃ ችግሩን እንደሚቀርፍ አረጋግጠዋል።
 በዋና መዲናዋ የሚኖረው የህዝብ ብዛት እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት የከተማ ልማት ሚኒስትሯ ኢ/ር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው፤ የቤት አቅርቦት በሚፈለገው መጠን እንዲሆን መንግሥት አዳዲስ ፖሊሲዎችን ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረው፣ በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች ግንባታው እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በቀደሙት ጊዜያት መንግሥት ከፍተኛ ወጪ ከሚያወጣባቸው መስኮች መካከል የኮንስትራክሽን ዘርፉ አንዱ እንደነበር የገለፁት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሀም በላይ ፤ የሃገር ኮርፖሬሽኑ በመደበኛ የግንባታ ሥርዓት መሥራቱን ቢቀጥል ኖሮ ከፍተኛ ወጪ እና ጊዜ ይወስድ የሚወስድ በመሆኑ፤  ሃገር በቀል ተቋራጮችን ከውጭ ቴክኖሎጂ ድርጅቶች ጋር በማጣመር ለመሥራት ሚኒስትር መ/ቤቱ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ በአዲስ ቴክኖሎጂ ይገነባሉ የተባሉት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ከ8 ሺኅ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር፣ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን በግንባታ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ለሚያደርጉ 20 የማስተርስ ተማሪዎች ወጪያቸውን በነፃ ለመሸፈን መታቀዱም ተሰምቷል።

LEAVE A REPLY