ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዞር እና ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በዘርፉ ለመሰማራት የፈለጉ የውጭ አቻ ኩባንያዎች ምዘና በመጠናቀቁ ዘርፉን ለመምራት አማካሪ ድርጅት መቀጠሩ ተነገረ።
የኢትዮጵያ ቴሌኮምን አገልግሎት ለማቀላጠፍና ለማሻሻል ፈቃድ የሚሰጣቸው ኩባንያዎች የዋጋቸው ግምት ተሠርቶ መጠናቀቁ የተነገረ ሲሆን፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት የኢትዮጵያ መንግሥት በቴሌኮም ዘርፍ በሚያደርገው ሪፎርም ሂደት ዙርያ አወዛጋቢ ሪፖርቶች መሰማታቸው አይዘነጋም።
በቅርቡ የተሰራጩት አወዛጋቢ ሪፖርቶች ዙሪያ የተፈጠሩ ውዥንብሮችን ለማጥራት የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን በቅርቡ መግለጫ እንደሚሰጥ የተናገሩት ዶክተር እዮብ፤ በፕራይቬታይዜሽን እና ሊበራላይዜሽን ዙሪያ ብዙ ጊዜ ብዥታ መኖሩን ገልጸዋል።
የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ መሸጥ እና 2 አዳዲስ የውጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ሃገር ቤት ማስገባት የተለያዩ ሥራዎች እንደመሆናቸው፣ እነዚህን ለያይቶ ማየት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።
የቴሌኮም ሥራ እንዲሠሩ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ኩባንያዎች የሚሰጣቸው ፈቃድ ብዙ ዋጋ ተሰጥቶታል ያሉት ሓላፊው፤ ቴሌኮምን በከፊል ወደግል ለማዞር ሥራዎች ተጠናቅቀው ተወዳድሮ ያሸነፈው አማካሪ ድርጅት ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ለዚሁ ሥራ አዋጁ ሲዘጋጅ ጀምሮ በየጊዜው ከፍ ያለ ድጋፍ እያደረገ የቆየ ሲኾን፣ አሁንም እያደረገ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ ከሊበራላይዜሽን በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም ራሱ እንደ አንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ቁጥጥር የሚደረግበትም መሆኑ ተሰምቷል።
በቀጣይ በጉዳዩ ላይ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር እንደሚመክር፣ መንግሥት የጀመረውን የቴሌኮም ሪፎርም ሥራ እንደማያቆምና በብርቱ እንደሚጓዝበት ያስረዱት ሚንስትር ደኤታው፣ በዚህ ዙሪያ የተቀየረም ሆነ የሚቀየር ነገር የለም ሲሉ ገልጸዋል።