ታህሳስ ወር ላይ ኢትዮጵያ የምታመጥቀው 2ኛ ሳተላይት በድርቅ ላይ እንድትሠራ መታቀዱ ተነገረ

ታህሳስ ወር ላይ ኢትዮጵያ የምታመጥቀው 2ኛ ሳተላይት በድርቅ ላይ እንድትሠራ መታቀዱ ተነገረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ የምታመጥቀው ሳተላይት በዓይነቱ የተለየ መሆኑ ከወዲሁ እየተነገረለት ነው።

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው፤ በሚሸፍነው ቦታ፤ በተልዕኮውና በእድገት ዑደት ለየት የሚያደርጋትን  ET SMART RSS የተሰኘች ሳተላይት በ2013 ዓ.ም በመጀመሪያ አራት ወራት ውስጥ ለማምጠቅ የሚያስችላት የግንባታ ሥራ መጠናቀቁን የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ይፋ አድርጓል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ  በ2013 ዓ.ም ከታኅሣሥ ወር በፊት ሁለተኛዋንና በዓይነቷ የተለየች ሳተላይት ለማምጠቅ የግንባታ ሥራውን መጠናቀቁን ጠቁመው፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሃገራት ብዙ የኢኮኖሚና የልማት ችግራቸውን ለመፍታት ብዙ ሳተላይቶችን ማምጠቅ የሚጠበቅባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ኢንስቲትዩቱ ይህን እውን ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል።
ሳተላይትን ማምጠቅ ሀብት ማከማቸት መሆኑን ያስረዱት  ዋና ዳይሬክተሩ፤ በየጊዜው ሳተላይቶቹን የማሻሻል ተግባር ስለሚከናወን የሚገኘው መረጃም የጠራና ሠፊ እንደሚሆን አረጋግጠዋል።
  በቅርብ ወራት ውስጥ ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ ያለው ሳተላይት ከመጀመሪያዋ ሳተላይት ብዙ ለየት የሚያደርጓት ነገሮችን ያካተተችጨሲሆን በዋናነትም በቴክኖሎጂው፤ በሚሸፍነው ቦታ፤ በተልዕኮውና በእድገት ዑደቷ የተለየች መሆኗ ተነግሯል።
ሳተላይቷ ከመጀመሪያዋ ሳተላይት ሥራ በተጨማሪ በስፋት ከድርቅ ጋር ተያይዞ ትኩረት አድርጋ እንድትሠራ የታሰበ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከቀደመው ሳተላይት የተወሰዱ ልምዶችንም መተግበሪያ እንደምትሆን አብራርተዋል።
ET SMART RSS የተሰኘችው ሳተላይት የክብደት መጠኗ 12 ኪሎግራም እንዲመዝን ሆኖ መሠራቷ ደግሞ ህዋ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳያጋጥማት ስለሚያግዝ የተሻለ መረጃ በመላክ ሃገርን የመጥቀም ዕድል ይኖራታል ተብሏል።

LEAVE A REPLY