ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በእስልምና ሊቃውንት ላይ ያነጣጠረ ነው ያለውን ጥቃት እንዲቆም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ጠየቀ።
ትናንት ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ የሃይማኖት ሊቃውንት፣ ዑለማና ኢማሞች በጠራራ ጸሐይ በተከበሩ የአምልኮ ቦታዎች ሳይቀር ጥቃት እየተፈጸመባቸው ነው ብሏል።
በሰኔ ወር መገባደጃ ከተፈጸመው ከሃጫሉ ግድያ በኋላ የመስጂድ ኢማሞችና ታዋቂ ሰዎች በአርሲና በሃረር የተለያዩ ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሥራ አመራር ቦርድ ዋና ጸሓፊ ሃጂ ከማል ሃሩን ይፋ አድርገዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአርሲና ሐረርጌ የተለያዩ አካባቢዎች የመስጂድ ኢማሞች፣ ኡላማዎች እና በአካባቢው ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ጥቃት በተደጋጋሚ መሰነዘሩን ተከትሎ ጠቅላይ ምክር ቤቱ መግለጫ ለመስጠት መገደዱን ገልጿል።
መግለጫው የተሰጠው “ሰዉን ማረጋጋት የሁላችንም ሓላፊነት በመሆኑ፣ እንዲሁም ጉዳዩ መስመሩን የሳተ እንዳይሆን፣ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ ስጋት ስላለን ነው” ሲሉ ሐጂ ከማል ሀሩን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን ጉዳቱ በማን እንደደረሰ? መቼና ማን እንዳደረሰው? የማጣራት ሥራ እየተሠራ በመሆኑ ወደፊት ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጥበትም ተሰምቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙን ጠቁሞ ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም ቢሆኑ እንዲህ አይነት ጥቃትን በጋራ ማውገዝ ይገባቸዋል ብሏል።
የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ግድያ ከተፈፀመባቸው ስፍራዎች አንዱ ወደ ሆነው ምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ ሃሳሳ ወረዳ የልዑካን ቡድኑን ልኮ እንደነበር የተናገሩት ሃጂ ኢብራሂም፤ በስፍራው አሳሳ ከተማ አንድ ኢማም ከባለቤታቸው እና ከልጃቸው ጋር በታጣቂዎች መገደላቸውን በቦታው ከነበሩ የዓይን እማኞች መስማታቸውን ይፋ አድርገዋል።
በአርሲ ፣ በሐረርና በባሌም በእስልምና ሊቃውንትና ዑለማዎች ላይ የተለያዮ ጥቃቶች መድረሳቸውን የገለጸው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት በፍጥነት ሊቆም ይገባል ብሏል።