የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ እና ግድያውን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ ዞኖች ተቀነባብረው በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጎዱ ኦርቶዶክሳውያንን መርዳትንና መልሶ ማቋቋምን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ
“አማን አማን እብለክሙ ከመ ትበክዩ ወትላህዉ አንትሙ፤ ወዓለምሰ ይትፌሣሕ፤ ወአንትሙሰ ተኃዝኑ፤ ወኃዘንክሙ ፍሥሐ ይከውነክሙ =
እውነት እውነት እላችኋለኹ፤ እናንተ ታለቅሳላችኹ፤ ሙሾም ታወጣላችኹ፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተም ታዝናላችኹ፤ ነገር ግን ኃዘናችኹ ወደ ደስታ ይለወጣል፡፡” (ዮሐ.16፥20)
ሃጫሉ ሁንዴሳ ስመ ጥምቀቱ ኃይለ ገብርኤል፣ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በአዲስ አበባ መገደሉ ይታወሳል። ቤተ ክርስቲያን፥ በዚያ ድንገተኛ የልጇ ግድያ ከባድ ኃዘን ተሰምቷታል፡፡ ኾኖም፣ በግድያው የተሰማትን ኃዘን ለመወጣት ጊዜ ሳይሰጣት፣ ኃዘንተኛነቷ ተረስቶ እና እንደ ጠላት ተቆጥራ፣ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በክርስቲያን ልጆቿ ላይ ዘግናኝ ፍጅት እና መከራ ተፈጸመባቸው።
በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ በአሠቃቂ መልኩ በገጀራ ተቀሉ፤ በቆንጨራ ተቆራረጡ፤ በጦር ተወግተው በጩቤ ተዘከዘኩ፤ በሜንጫ ተተለተሉ፤ በዱላ ተቀጥቅጠው እና በደንጊያ ተወግረው ተገደሉ፤ አስከሬናቸው በጎዳና እየተጎተተ ሲንገላታ ዋለ፤ ለቀናት በየቦታው ወድቆ የቆየው የሰውነት ክፍላቸው ለከርሠ አራዊት ሲሳይ ኾነ፤ ሴቶች፥ በልጆቻቸው፣ በአባቶቻቸው እና በባሎቻቸው ፊት ተደፈሩ፤ ለዘመናት የደከሙበት ቤት ንብረታቸው፣ በጥናት እና በጥቆማ እየተለየ ከተዘረፈ በኋላ ቀሪው ጋዝ እየተርከፈከፈበት በእሳት እየጋየ ወደመ፤ ብዙዎች ከሞቀ ቀዬአቸው ተፈናቅለው የክረምቱን ጨለማ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን በሚገኙ መቃብር ቤቶች እና አዳራሾች፣ በልዩ ልዩ መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም፣ በግሰለቦች ቤቶች ተጠልለው ለማሳለፍ ተገደዱ፤ ለአስከፊ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቡናዊ ቀውሶች ተዳረጉ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን፣ ይህንኑ የተቀነባበረ ጥቃት እንደሰማች፣ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በቋሚ ሲኖዶስ የሐዘን መግለጫ አውጥታለች፤ በአገር ውስጥ እና በውጭ በሐዘንና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ስታመለክት ከርማለች፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም፥ “አጥፊዎችን አንታገሥም፤ ተገቢውን ፍትሕ እንሰጣለን፤ የተጎዱትን እንክሳለን፤” ብለው ቃል የገቡትን ይፈጽሙ እንደ ኾነ በማለት በትዕግሥት ጠብቃ ነበር፡፡ ኾኖም፣ ዜጎችን ከጥቃት አስቀድሞ የመከላከል እና የመጠበቅ፣ ፍትሕን የማስፈንና ተጎጂዎችን በአግባቡ የመካስ ሓላፊነታቸውን በወቅቱ እና በብቃት ሲወጡ አላየችም፡፡
በጉዳዩ ላይ የተወያየው ቋሚ ሲኖዶስም፣ በየሥፍራው በአካል ተገኝቶ የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ዐቢይ ኮሚቴ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንዲቋቋም መመሪያ ሰጥቷል፡፡ በዚኽም መሠረት ዐቢይ ኮሚቴው፣ ተጎጂዎችን፥ በጊዜያዊነት ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ንኡሳን ኮሚቴዎችን አደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
ዐቢይ ኮሚቴው ባወጣው መርሐ ግብር፣ የሥራው መጀመሪያ ያደረገው፣ ጥቃቱ የተፈጸመባቸውን አካባቢዎች በዝርዝር በመለየት፣ ተጎጅዎችን የማጽናናት እና መረጃ የማሰባሰብ ጉዞ ማካሔድ ነበር፡፡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ መንፈሳውያን ማኅበራትንና በርካታ የብዙኃን መገናኛዎችን ጨምሮ 260 ያኽል ልኡካን የተሳተፉበት ይኸው ጉዞ፣ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች ውስጥ በስድስት አህጉረ ስብከት የሚገኙ 25 ወረዳዎችን የሸፈነ ነበር፡፡
የዐቢይ ኮሚቴው ልኡካን፣ ተጎጂዎችንና በማነጋገር እና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች በመጎብኘት ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ የልጃችን የኃይለ ገብርኤልን ግድያ ተከትሎ፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ የመንግሥትን መዋቅር ተገን ያደረጉ የእምነት እና የብሔር ጽንፈኞች አስቀድመው ከተደራጁ ኀይሎች ጋራ በመቀናጀት የፈጸሙት ስልታዊ እና አረመኔያዊ ጥቃት ዋና ዒላማ፣ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን እንደነበሩ ተረጋግጧል፡፡
ከሰኔ 22 ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት በተፈጸመው በዚያ ጥቃት፥ ከ67 በላይ ምእመናን በግፍ እና በአሠቃቂ ኹኔታ ተገድለዋል፤ 38 ምእመናን ቋሚ(ከባድ)፣ 29 ምእመናን ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ከሰባት ሺሕ በላይ ምእመናን ከመኖሪያቸው ከመፈናቀላቸው ባሻገር፣ በተለያየ ደረጃ ለሚገለጽ ሥነ ልቡናዊ እና ሥነ አእምሯዊ ቀውስ ተዳርገዋል፤ ከአምስት ቢልዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረታቸውንም በዘረፋ እና በቃጠሎ ማጣታቸውን፣ ከዐቢይ ኮሚቴው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡
የጥቃቱን አስከፊነት በዚኽ መልኩ የተረዳው ዐቢይ ኮሚቴው፣ ተጎጅዎችን በአፋጣኝ ባሉበት ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም ይቻል ዘንድ፣ አደረጃጀቱን በዐዲስ መልክ በማጠናከር ተልእኮውን በአጭር ጊዜ ለማከናወን የሚያስችለውን ስልት ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የጉዳቱን መጠን በነፍስ ወከፍ ደረጃ የመለየት ሥራ እየሠራ ሲኾን፣ በዚኽም መነሻነት፣ ርዳታው በቀጥታ ለተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲደርስ ይደረጋል፤ በዘላቂነት ለማቋቋምም ኹኔታዎችን ያመቻቻል፡፡
ዐቢይ ኮሚቴው፣ በጉዳት ጥናት መረጃው መሠረት፣ ጊዜያዊ ርዳታን ከማድረስ እና ከመልሶ ማቋቋም ባሻገር፣ መንግሥት በአስቸኳይ ሊፈጽማቸው የሚገቡ ተግባራት አሉ ብሎ ያምናል፤ እነዚኽም፤
ተጎጅዎች በሃይማኖታቸው በደረሰባቸው ስልታዊ እና ዘግናኝ ጥቃት የተነሣ፣ በከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ላይ እንደሚገኙ በቀረበው ሪፖርት እና ማስረጃ አረጋግጠናል፡፡ በወቅቱ ያሉበት ኹኔታ፣ ለኮሮና ቫይረስ እና ለሌሎችም ተላላፊ በሽታዎች የሚያጋልጣቸው እንደኾነ ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በመኾኑም፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የፌዴራል መንግሥት፣ የኦርቶዶክሳውያን ኢትዮጵያውያንን በሕይወት የመኖር እና ሀብት የማፍራት ሰብአዊ እና ዜግነታዊ መብቶችን በማስከበር፣ የደኅንነት እና የኑሮ ዋስትና በአፋጣኝ እንዲያረጋግጥላቸው ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች፡፡
መንግሥት፥ ጥቃቱን ያቀዱትን፣ የፈጸሙትንና ያስተባበሩትን ኀይሎች እንዲሁም፣ የተጣለባቸውን ሓላፊነት ወደ ጎን በማለት ጥቃቱን በዝምታ የተመለከቱትን በመዋቅሩ ውስጥ ያሉትን ሹማምንት እና የጸጥታ አካላት የኾኑ አጥፊዎችን፣ በቁጥጥር ሥር በማዋል እና በሕግ ተጠያቂ በማድረግ ፍትሕ ርትዕ እስከ መጨረሻው እንዲያሰፍን ታሳስባለች፡፡ በዚኽ ረገድ፣ መንግሥት፣ ከጥቃቱም በኋላ ቢኾን፣ ሕግን ለማስከበር እያደረገ ያለውን ጥረት፣ ቤተ ክርስቲያን በቅርበት የምትከታተለውና የምታደንቀውም ነው፤ ለውጤታማነቱም፣ ማናቸውንም የበኩሏን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኗን ትገልጻለች፡፡
በአሳዛኝ ኹኔታ በደል እና ግፍ የተፈጸመባቸው ኾነው እያለ፣ በጥቃቱ ምንም ሱታፌ የሌላቸው ንጹሐን ዜጎች፣ በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ ታስረው እየተንገላቱ በመኾኑ፣ ጉዳያቸው በጥንቃቄ ታይቶ ከእስር እንዲፈቱ ታሳስባለች፡፡
አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የፖሊቲካ ፓርቲዎች፥ የግፉዓን ሰማዕታቱን መጠቃት፣ አላግባብ ለቡድናዊ እና ፖሊቲካዊ ትርፍ በመጠቀም በሐዘናችን ከመሣለቅ እንዲቆጠቡ፤ መንግሥትም፣ ተገቢውን ክትትል በማድረግ እንዲያስታግሥ ቤተ ክርስቲያን አበክራ ታሳስባለች፡፡
ከወርኀ ሰኔው ጥቃት በፊትም ኾነ በኋላ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሱ የሚገኙ ስልታዊ የኾኑ ግልጽ ተጽዕኖዎች እና ጥቃቶች፣ በዐይነት እና በመጠን እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ አብዛኞቹ የክልል መንግሥታት፣ ለውይይት ባሳዩት በጎ ፈቃድ፣ ጥቃቱንና ተጽዕኖውን በተወሰነ ደረጃ ለመግታት ቢቻልም፣ በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የወቅቱ አስተዳደር ግን፣ የቀረበለትን በጋራ ችግሮችን የመፍታት ጥያቄ ችላ በማለት እና ባለመቀበል ቤተ ክርስቲያናችንን በተደጋጋሚ አሳዝኗታል፡፡ በክልሉ የተወሰኑ አህጉረ ስብከት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያገደው ሕገ ወጥ ቡድን፣ ለቤተ ክርስቲያን በሕግ የተሰጧትን መብቶች ከመጋፋት ጀምሮ የአስተዳደር መዋቅሯን እስከ ማፍረስ የተዳፈረው፣ ክልላዊ መንግሥቱ ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠት በሚያሳየው ቸልተኝነት እንደ ኾነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ በመኾኑም፣ የትላንቱን ችግር ለማከም፣ ይልቁንም ነገ በከፋ መልኩ ሊመጣ ያለውን ለማስቀረት እንዲቻል፣ በጋራ ከመሥራት ውጪ መፍትሔ የለም፤ ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ ክልላዊ መንግሥቱ፣ ጥያቄያችንን ተቀብሎ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንዲኾን ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች፡፡
በ2012 ዓ.ም. መባቻ፣ በአንድ ቀን 97 ዜጎች እና ምእመናን ካለቁበት የወርኀ ጥቅምቱ ጥቃት እንዲሁም የወርኀ ጥር የበዓለ ጥምቀት አከባበር ወቅት ከተፈጸሙ ግድያዎች እና ዘረፋዎች ጀምሮ፣ በልዩ ልዩ የአገራችን አካባቢዎች፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየደረሱ ያሉ ግፎችንና በደሎችን መንግሥት አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ፣ ውጤቱንም በይፋ ለሕዝብ እንዲገልጽ ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ትጠይቃለች፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ለአገር ሰላም እና ለሕዝብ አንድነት ባበረከተችው አስተዋፅኦ፣ በገነባችው የተቀደሰ ባህል እና ባወረሰችው ዘርፈ ብዙ እሴት፣ በኢትዮጵያውያን ኹሉ ልትከበር እና ልትወደድ የሚገባት ናት፡፡ ከሞላው ጸጋዋ እና በረከቷ ያልተቋደሰ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ተብሎ የማይገመት በመኾኑ፣ የኹሉ እናት እና ባለውለታ ናት ብለን እናምናለን፡፡
ኾኖም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሱ ያሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ አብዝቶ እንደሚነገረው፣ “በሽግግር ወቅት የሚያጋጥሙ” ተብለው ብቻ የሚታለፉ ሳይኾኑ፣ የተሳሳቱ ርእዮተ ዓለማዊ ትርክቶችንና ጂኦ-ፖለቲካዊ ዳራዎችን መነሻ በማድረግ በተቀነባበረ እና በተደራጀ ስልት የሚፈጸሙ ኦርቶዶክሳውያንን የ‘ማጽዳት’ እንቅስቃሴዎች እንደኾኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየኾነ መምጣቱን ቤተ ክርስቲያናችን ትገነዘባለች፤ በአጭር ጊዜ ሳይታረም በዚኹ ከቀጠለም፣ የከፋ ፍጻሜ ሊያስከትል እንደሚችል ከወዲሁ ታስገነዝባለች፡፡
ስለዚህም፣ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት፥ በእኒህ ስሑት አስተሳሰቦች እና ሐሳዊ ትርክቶች ማሕቀፍ፣ ኾነ ተብሎ የሚፈጸም ኦርቶዶክሳውያንን የማሣቀቅ እና የማዳከም ሃይማኖት ተኮር ጥቃትን አስቀድሞ በመከላከል፣ ፍትሕን በማስፈን፣ ተጎጂዎችን በአግባቡ በመካስ እና በማቋቋም፣ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በአጽንዖት ታሳስባለች፡፡
የተወደዳችኹ ተጎጂ ምእመናንና ምእመናት የመንፈስ ልጆቻችን፤
የግፍ ጥቃቱ የደረሰባችኹና በአሁኑ ወቅት በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን አዳራሾች እና በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ተጠልላችኹ እንደምትገኙ ይታወቃል፡፡ ይህ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችኹ የተቀበላችኹት መከራ፣ በቤተ ክርስቲያናችን የሰማዕታት መዝገብ በወርቅ ቀለም ተጽፎ የሚኖር ነው፡፡ በግፈኞች ፊት ለማዕተበ ክርስትናችኹ ታምናችኹ ባሳያችኹት ጽናት እና በከፈላችኹት መሥዋዕት፣ የአገራችኹን ህልውና እና አንድነት ታድጋችኋል፤ የቤተ ክርስቲያናችኹን ልዕልና አስመሰክራችኋል፡፡ ይኸውም፣ ለትውልድ አብነት ኾኖ በምሳሌነት ሲነገር የሚኖር በመኾኑ፣ እናት ቤተ ክርስቲያናችኹ ኮርታባችኋለች፡፡ ለወደፊትም፣ መላው ኢትዮጵያውያንና ኦርቶዶክሳውያን፣ በሚያስፈልጋችኹ ኹሉ ከጎናችኹ ይቆማሉ፤ ብቻችኹን እንዳልኾናችኹም ቤተ ክርስቲያን ታረጋግጥላችኋለች፡፡ ዛሬ ባገኛችኹ መከራ ግፍ አድራሾች ቢደሰቱም፣ በጊዜው ጊዜ ፍትሕን በሕግ ተጎናጽፋችኹ እንባችኹ እንደሚታበስ እና ኃዘናችኹ ወደ ደስታ እንደሚለወጥ ቤተ ክርስቲያናችን ታምናለች፡፡
በአገር ውስጥ እና በውጭ የምትገኙ የተወደዳችኹ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
አሠቃቂው ጥቃት ከደረሰበት ሰዓት ጀምሮ፣ በኢትዮጵያዊ ነባር አስተምህሮ እና የአብሮነት ባህል እርስ በርስ በመረዳዳት፣ ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ያሳደረው ከባድ የኑሮ ጫና ሳይበግራችኹ እና ርቀት ሳይገድባችኹ የጥቃቱን ሰለባዎች ለመታደግ እና መልሶ ለማቋቋም ያደረጋችኹትንና በማድረግ ላይ ያላችኹትን ልዩ ልዩ አስተዋፅኦ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በከፍተኛ አንክሮ ትመለከታዋለች፤ የጎሣ እና የእምነት ልዩነት ሳይገድባችኹ እስከ ሞት ደርሳችኹ ላደረጋችኹት ሰብአዊ እና ኢትዮጵያዊ ርዳታ እና ድጋፍ፣ ልዑል እግዚአብሔር ዋጋችኹን ይከፍላችኹ ዘንድ ዘወትር ትጸልያለች፡፡
በሌላ በኩል፣ በክርስቲያናዊ የትብብር መንፈስ፣ በኦርቶዶክሳውያን ላይ የደረሰው ጉዳት ተሰምቷችኹ፣ ጥቃቱን በማውገዝ አጋርነታችኹን በመግለጫ እና በልዩ ልዩ ድጋፎች ላሳያችኹ የዓለም ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የከበረ ምስጋናዋን ታቀርብላችኋለች፡፡
አሁንም፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተጠናክሮ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት፣ ተጎጅዎችን ለመርዳት እና በዘላቂነት ለማቋቋም እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ፥ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በሞያ እንድትድገፉ፤ እንዳስፈላጊነቱም በቀጣይነት ለሚያስተላልፈው ጥሪ ንቁ ምላሽ ለመስጠት እንድትዘጋጁ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ በዚኹ አጋጣሚ፣ በአገር ውስጥ እና በውጭ የምትኖሩ ምእመናን፥ ድጋፍ እና አስተዋፅኦ ማድረግ ያለባችኹ፣ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው የርዳታ አሰባሳቢ አካል በከፈታቸው የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች ብቻ መኾኑን እናስታውቃለን፡፡
ቸሩ እግዚአብሔር፥ ለአገራችንና ለዓለም ሰላምን፣ ለሕዝባችን አንድነትን፣ በግፍ ለተገደሉት ልጆቻችን ዕረፍተ ነፍስንና ለቤተ ክርስቲያናችን መጽናናትን እንዲሰጥልን እንለምናለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት