25 ሺኅ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሰሞኑን ወደ ሀገር ቤት ሊመለሱ ነው

25 ሺኅ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሰሞኑን ወደ ሀገር ቤት ሊመለሱ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከ25 ሺኅ በላይ ኢትዮጵያዊያን በቅርቡ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ይደረጋል ተባለ።

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አብዱልአዚዝ አህመድ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ በከፋ ችግር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
ይህን ተከትሎ በችግር ውስጥ የሚገኙትን ኢትዮጵያዊያን ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ከሳዑዲ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት አምባሳደሩ፤ በቅርቡም ከ20 ሺኅ በላይ ዜጎች መንግሥት ያወጣውን የኮሮና ወረርሽኝ መመሪያ በማሟላት ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ኖሯቸው በሥራ ላይ የነበሩ ዜጎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስሥራቸው በመቀዛቀዙ ችግር ውስጥ መግባታቸውን አያይዘው የገለጹት አምባሳደሩ፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሳዑዲ የምግብ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር ስደተኞቹ በየቤታቸው ምግብ እንዲደርሳቸው መደረጉን አስረድተዋል።
በተያያዘ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ የጠቆሙት አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ፤ ከእነዚህም ውስጥ 5 ሺኅ የሚሆኑትን ወደ አገራቸው ለመመለስ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ስራ የፈቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቤይሩት መጠለያ እንደሚገኙ የተናገሩት አምባሳደሩተ፤ በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን መብት ለማስጠበቅ ከአገሪቷ መንግሥት ጋር ምክክር እየተደረገ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

LEAVE A REPLY