ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ቁጥራቸው 60 የሚደርሱ የታጠቁ የትግራይ የልዩ ኃይል አባላት ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን የአማራ ክልል ቢገልጽም፤ የትግራይ ክልል በበኩሉ ወሬው ከእውነት የራቀ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ከትግራይ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ወደ አማራ ክልል እየመጡ መሆኑን የጠቆሙት የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዮኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ፤ 60 የሚሆኑ የታጠቁ የልዩ ኃይል አባላት ወደ ክልሉ ከነትጥቃቸው መግባታቸውን ገልጸዋል።
የልዮ ኃይል አባላቶቹ ከወልቃይት፣ ከራያ አካባቢ የመጡ አማራ የሆኑ እና አብዛኛዎቹ ደግሞ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን ያብራሩት ሓላፊው የአማራ ክልል መንግሥት አባላቱን ተቀብለው ትጥቅ በማስፈታት በአንድ ካምፕ ማስቀመጣቸውንም ይፋ አድርገዋል።
የትግራይ የክልል የሕዝብና መንግሥት ግንኙነት ቢሮ ምክትል ኃፈሓላፊ አቶ ሐዱሽ ካህሱ፤ “ይህ የበሬ ወለደ ንግግር ካልሆነ በስተቀር እውነት አይደለም” ሲሉ ጉዳዮን አስተባብለዋል።
“ምናልባት ከአማራ ክልል ወደ ትግራይ ነው እየሄደ ያለው የሚለውን እነርሱ ይመልሱ እንጂ፤ ከትግራይ ወደ አማራ ክልል የሚሄድ የለም” ሲሉም አንድም የትግራይ ክልል ልዮ ኃይል አለመኮብለሉን አስረግጠው ተናግረዋል።
የማንነት እና ወሰን ጥያቄን የአማራ ክልላዊ መንግሥት ትቶታል የሚለው ትክክል አይደለም በማለት የሚከራከሩት አቶ ግዛቸው፤ የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄዎች እያነሳ እንደሚገኝ አስታውሰው፤ የማንነት እና ወሰን፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ ሃቀኛ ፌደራሊዝም ትግበራ እና ሌሎችም አቋም የተያዘባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
“በወልቃይት እና ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ያነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች አፈና፣ እስራት እና እንግልት እየደረሰባቸው ነው” ያሉት ሓላፊው፤ ይህንን ለማስመለሰም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ክልሉ ይንቀሳቀሳል ከማለታቸው ባሻገር፤
“ህወሓት ምርጫ አካሂዳለሁ” ብሎ ሕዝቡን መከራ እያበላ ነው። ችግሩ ከዚህ በላይ እየከረረና አደብ የማይገዛ ከሆነ ፌደራል መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር የሚያስችል አቅምና ሥልጣን ስላለው፤ በዚህ መሠረትም ህወሓትና የትግራይ ሕዝብን በመለየት ሕግ የማስከበር ሥራ ሊሠራ ይገባል” ብለዋል።