ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በያዝነው 2012 ዓ.ም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለ133 ሺኅ 459 መዛግብት እልባት መሥጠት እንደተቻለ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ ገለጹ።
በዓመቱ የፍርድ ቤቶችን የማጥራት አቅም 98 ነጥብ 2 ለማድረስ ተችሏል ብለዋል።
ፍርድ ቤቶች ዋነኛ ተልዕኮ በሆነዉ የመዛግብት አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ ጥራታቸዉን ጠብቀዉ እልባት መሥጠት እንዲቻል ተሠርቷል ያሉት ወ/ሮ መዓዛ፤ እልባት ከተሠጠባቸዉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት 15 ሺኅ 576 መዝገቦች ዉስጥ 94 ነጥብ 8 በመቶ ከአንድ ዓመት ያነሰ ቆይታ ያላቸዉ መዝገቦች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በዳኝነት ሥራዎች በ2012 ዓ.ም ፆታዊ ጥቃትን በተመለከቱ 302 ጉዳዮች ላይ ዉሳኔ ተሰጥቷል፡፡ ከእነዚህ መሀል 44 ዉሳኔዎች ፍርድ ቤቱ በኮቪድ-19 የኮሮና ቫይረስ መከሠት ምክንያት በከፊል በተዘጋበት ግዜ የተሠጡ መሆናቸው ታውቋል።
የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኘነትና ተጠያቂነትን ማጎልበት የሚያስፈልጉ የአደረጃጀት ማሻሻያዎች ስለመደረጋቸውም ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ተናግረዋል።