ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዛሬ ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደውን የመሬት ወረራ አስመልክቶ ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የተከለከለው ያልተሟላ መስፈርት በመኖሩ ነው ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ፓርቲው መግለጫውን እንዳይሰጥ የተከለከለው ማሟላት የነበረበትን መስፈርት ባለማሟላቱ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ያለችው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኑን ያስታወሱት ዋና ኢንስፔክተሩ፤ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ስብሰባዎች መካሄድ ያለባቸው ለኮሮናቫይረስ በማያጋልጥ ሁኔታ ነው ብለዋል።
ይህንን ባላሟላ መልኩ ስብሰባዎችን ማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መጣስ በመሆኑ ፖሊስ ስብሰባውን መከልከሉን የጠቆሙት ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ፤
“ፓርቲው ፈቃድ ስላለገኘ ፈቃድ በሚያገኙበት ወቅት ጥበቃም ስለሚደረግላቸው ያኔ ስብሰባውን ማካሄድ ይችላሉ” በማለት ተናግረዋል።
ኢዜማ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከመሬት ወረራና ከኮንዶሚኒየም እደላ ጋር በተያያዘ ለረጅም ጊዜ ያደረገውን ጥናት በተመለከተ በማስረጃ የተደገፈ መግለጫ ለሚዲያና ለሕዝብ ለመስጠት አስፈላጊውን መስፈርት ማሟላቱን አስታውቋል።
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ናትናኤል ፈለቀ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ኢዜማ ለቤቶች ልማት ኤጀንሲ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ እንዲሁም ለመሬት ልማት ቢሮ ደብዳቤ ቢያስገባም የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ደብዳቤውን ተቀብሎ ምላሽ እንዳልሰጠ ከመጠቆሙ ባሻገር ሁለቱ ጉዳዮ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ደብዳቤውን ለመቀበል ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ጭምር ይፋ አድርጓል።