ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ፤ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የተገነባው የኮቪድ-19 ፊልድ ሆስፒታል ጳጉሜን 5 ሥራ ይጀምራል ተባለ።
በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋቱን ተከትሎ በአፋጣኝ የተገነባውን ሆስፒታል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እና ከሌሎች መንግሥታዊ ባለሥልጣናት ጋር ጎብኝተውታል።
በለይቶ ማቆያነት የሚያገለግለው ሆስፒታል በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስር፤ በጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት በዓለም ምግብ ፕሮግራምና በዓለም ጤና ድርጅት ድጋፍ የተገነባ መሆኑም ተሰምቷል።
ሆስፒታሉ ጳጉሜ 5 ቀን ሥራ እንደሚጀምር የተናገሩት የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ታምሩ አሰፋ ፤ ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምርም 200 አልጋ እንደሚኖረውም ይፋ አድርገዋል።