ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ የ20/80 እና 40/60 ተመዝጋቢ ሆነው ቤት ያልደረሳቸው ነዋሪዎች በማኅበር ተደራጅተው የጋራ ቤት ለመገንባት እንዲችሉ አማራጭ የመፍትሄ ሀሳብ ቀረበ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ዛሬ 30ኛ መደበኛ ጉባዔውን ሲያካሂድ በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ቢወያይም፣ በከተማዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤትና የትራንስፖርት ችግር ከመፍታት አንፃር አፅንዖት ሰጥቶ መወያየቱ ተሰምቷል።
የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ ለ20/80 እና 40/60 ተመዝጋቢ ሆነው ቤት ያልደረሳቸው ነዋሪዎች በማኅበር ተደራጅተው የጋራ ቤት ለመገንባት እንዲችሉ ከተማ አስተዳደሩ የመሬት እና የግንባታ ግብዓት በማቅረብ እራሳቸው እንዲገነቡ ለማድረግ አማራጭ የመፍትኄ ውሳኔ ከተማ አስተዳደሩ ማሳለፉ ታውቋል።
በተጨማሪም በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ 400 አውቶቢሶች ግዢ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን እና በብልሽት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ 125 አውቶቡሶች በአስቸኳይ ጥገና ተደርጎላቸው ከአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀናት ጀምሮ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ካቢኔው ወስኗል።
ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራና የኮንዶሚኒየም እደላ በተረኞች የፖለቲካ ዘመቻ የተፈጸመበት የአዲስ አበባ መስተዳደር በታከለ ኡማ የሥልጣን ዘመን የሠራውን ይህንን ስህተት በተመለከተ በማስረጃ የተደገፈ ጋዜጣዊ መግለጫ ነገ በኢዜማ የሚሰጥ መሆኑ ያሰጋው የከተማ አስተዳደሩ ይህንን እውነታ ለመሸፋፈን ዛሬ ይህንን መግለጫ መስጠቱ በበርካቶች ዘንድ እየተነገረ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ለከተማዋ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቦታ በእጅጉ የተጨነቀ ቢሆን ኖሮ ከዚህ ቀደም ብሎ ይህን ሀሳብ በአማራጭነት የማቅረብ ሠፊ እድል ነበረው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች የዛሬው የአዳነች አቤቤ መግለጫ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ታስቦ የተሠራ ነው በማለት አስተያየት ሰጪዎች እቅዱን አጣጥለዋል።