ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በቢሾፍቱ ከተማ ሽብር በማስተባበርና በመደገፍ ተጠርጥረው ተይዘው የቆዩት የአቶ ልደቱ አያሌውን ጉዳይ ሲመለከት የነበረው ፍርድ ቤት የቀረበባቸው ጉዳይ አያስከስስም በሚል መዝገቡን መዝጋቱን ቢያሳውቅም አቶ ልደቱ ግን እስካሁን አለመፈታታቸው ተሰማ።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ዛሬ ጠዋት በቀጠሯቸው ቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፤ ችሎቱ ፖሊስ እስካሁን አለኝ ብሎ ያቀረበው የምርመራ ውጤትን አቅርቧል። ፍርድ ቤቱ የቀረበው ማስረጃ አቶ ልደቱን አያስከስስም ብሎ መዝገቡን እንደዘጋ የኢዴፓ የወቅቱ ሊቀመንበር አቶ አዳነ ተናግረዋል።
ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ችሎቱን የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቆ ነበር። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል።
አቶ ልደቱን የሚያስከስስ ማስረጃ አላገኘሁም በሚል ችሎቱ ጉዳዩን ቢቋጨውም፤ አቶ ልደቱ እስካሁን እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ እንዳልተለቀቁ የጠቆሙት አቶ አዳነ፤ አባላቸው ከእስር እንዲወጡ ነገ ሁለት ማመልከቻዎችን ሊያስገቡ ማሰባቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።