ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኦሮሚያ በቦረና ዞንክልል የታመመ ግመል አርደው ስጋውን ተካፋፍለው የበሉ 110 ጎረቤታሞች ሰዎች መታመማቸው ተሰማ።
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ የታመመ ግመል ስጋ ተመግበው ሕመም ያጋጠማቸው ሰዎች ቦርቦሪ ተብሎ በሚጠራ ጤና ጣቢያ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ነው የተሰማው።
የመጨረሻዋ ታማሚም እሁድ እለት በጤና ጣቢያ ውስጥ የሚደረግላትን ሕክምና አጠናቃ ከማዕከሉ መውጣቷ ቢታወቅም በሰዐቱ ከመቶ በላይ ሰዎች ለከባድ ሕመም ተዳርገው ነበር ተብሏል።
የግመሉን ስጋ ተመግበው ከታመሙ ሰዎች መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ቦሪ ጃርሶ፤ ስጋውን አብስለው ቢመገቡም ለህመም መዳረጋቸውን ነው የገለጹት።
“ባለ ግመሉ ሰውዬ ጎረቤታችን ነው። ግመሉ ሲታመም የተለያየ ባህላዊ መድኃኒት ሲያጠጡት ነበር። ግመሉ ግን ሕመሙ እየተባባሰበት ሲሄድበት ታረደ። ለእኛም ስጋው ተልኮልን ተካፍለን በላን” ሲሉም ግለሰቧ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ስጋውን አብስለው የተመገቡ ሰዎች ጨምሮ በሙሉ በሰዐታት ልዩነት ውስጥ መታመማቸውን የገለጹት ወ/ሮ ቦሪ፤ “ራስ ምታት እና ማስመለስ ያለው ከፍተኛ ሕመም ነው ያስከተለብን። ፈጣሪ እና ሐኪም ነው ያዳኑን እንጂ ከፍተኛ ህመም ነበር ያጋጠመን። አሁንም ድረስ የሕመሙ ሰሜት ከውስጣችን አልወጣም” ብለዋል።
በቦርቦር ጤና ጣቢያ ነርስ የሆኑት አቶ ኮከብ መሐዲ በቅድሚያ ወደ 20 የሚጠጉ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ታመው መምጣታቸውን አስታውሰው፤ “እንደ ተቅማጥ፣ ማስመለስ እና የሰውነት ሙቀት ያሉ ተመሳሳይ ምልክት ይታይባቸው ነበር” ሲሉም አጋጣሚውን ገልጸው በተመሳሳሳይ በአጠቃላይ 110 ሰዎች ማከማቸውን ይፋ አድርገዋል።
የታመመውን የግመል ስጋ በልተው የታመሙ ሰዎች በእድሜ ከ1 ዓመት እስከ 70 ድረስ እንደሆኑ ያስታወሱት አቶ ኮከብ ለታመሙ ሰዎች በተሰጠው ህክምና የሰዎች ህይወት እንዳለለፈም አረጋግጠዋል።
ማኅበረሰቡ የታመሙ እንስሳት ስጋ እና ጥሬ ስጋን መመገብ ማቆም ይኖርበታል ያሉት በቦረና ዞን ዳሲ ወረዳ የእንስሳት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ፍራኦል ዋቆ፤ “የእንስሳት በሽታ በሰው ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እንስሳት የሚታመሙት የተመረዘ ነገር በልተውም ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ በሰው ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላል። እንስሳት መድሃኒት ወስደው ከሆነ ደግሞ ከማረዳችን በፊት መድኃኒቱ ከሰውነታቸው እስኪወጣ መጠበቅ ይኖርብናል” በማለት ምክር ለግሰዋል።