በጋምቤላ ነዋሪዎች በአንበሳ እየተበሉ ነው ተባለ

በጋምቤላ ነዋሪዎች በአንበሳ እየተበሉ ነው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በጋምቤላ ክልል አቦቦ ወረዳ ባለፉት 12 ወራት ብቻ የአንበሳ ቡድን 5 ሰዎችን መብላቱን እና በአንድ ሰው ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት ማድረሱ ተነገረ።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ኡሞ ቱቶ የአንበሳው ቡድን በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመጥቀስ የፌደራል የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን እርምጃ አንዲወስድ ቢያሳውቁም፤ እርምጃ ባለመወሰዱ አሁንም አንበሳ በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል።
“እንደ ክልል አንበሳ መግደል አንችልም። ሪፖርት ማድረግ ብቻ ነው የምንችለው” ያሉት የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን የኅብረተሰብ አጋርነት እና የዱር እንስሳት ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ካህሳይ ገ/ትንሳዬ ፤ አጥፊው ቡድን ላይ እርምጃ የሚወስድ ቡድን ልከን አንድ አጥፊ ብቻ ነው የተቀነሰው በማለት ተናግረዋል።
አቶ ኡሞ በሚያስተዳድሩት ወረዳ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በአንበሳ ቡድኑ ጥቃት የደረሰው በተመሳሳይ በሐምሌ እና ነሐሴ ወራቶች እንደሆነ ገልጸዋል።
አምና ሁለት ሰዎች የተበሉት ሐምሌ እና ነሐሴ ወር ላይ ነበር። ዘንድሮም በሰዎቹ ላይ ጥቃት የደረሰው በሐምሌ እና ነሐሴ ወር ነው ያሉት አቶ ኡሞ ይህ የሆነበትን ምክንያት ግን ለእነርሱም እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።
 በቅርቡ በአንበሳ የተበላው በሰሊጥ እርሻ ላይ በቀን ሠራተኛነት የሚተዳደር እና እድሜው ወደ 30 ዓመት የሚጠጋ ወጣት ሲሆን፤ ቅዳሜ ነሐሴ 23/2012 ከሥራ ወጥቶ በመንገድ ላይ እየተጓዘ ባለበት በአንበሳ መበላቱን ሓላፊው አብራርተዋል።
ባለፈው ወር ላይም በአንበሳ የተበላው ግለሰብ በእርሻ ልማት ላይ የቀን ሠራተኛ ሆኖ የሚሠራ ሰው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኡሞ፤ በቅርቡ በአንበሳ ከተበሉት መካከል አንደኛዋ ሴት መሆናቸው እና እርሳቸውም ከምሽቱ 12 ሰዓዐት አካባቢ በመንገድ በእግር እየሄዱ  በአንበሳ መበላታቸውን አረጋገጠዋል።
“ሴትየዋ ወደ ሌላ ቀበሌ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆና እየሄደች ነበር። ብቻዋን ወደ ኋላ ስትቀር ነው የተበላችው” የጠቀሱት አስተዳዳሪ፤ ከባድ ጉዳት ያጋጠመው ግለሰብ ደግሞ መቀመጫው ላይ በአንበሳው ክፉኛ መነከሱን እና የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል ብለዋል።

LEAVE A REPLY