የዎላይታ ዞን አመራሮች ክስ እንዲቋረጥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ሊቀርብ ነው

የዎላይታ ዞን አመራሮች ክስ እንዲቋረጥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ሊቀርብ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በዎላይታ ዞን የተፈጠረውን አለመረጋጋት በተመለከተ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ለመነጋገር ያቀኑ የዞኑ ተወላጆች ሀሳባቸው ሳይሳካላቸው መመለሳቸው ተሰማ።

ከአካባቢው ህዝብ ጋር ለመመምከር ከደቡብ ክልልና ከፌደራል ከፍተኛ የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን ወደ ሶዶ ከተማ  የተጓዙት በችግሩ ላይ ለመምከር ቢሆንም የአካባቢው ተወላጆች ከውይይቱ በፊት የታሰሩት የዞኑ አመራሮች ሊፈቱ ይገባል የሚል ወጥ አቋም በመያዛቸው ጥረቱ እንዳልተሳካ ለመረዳት ችሏል።
ችግሩን እንፈታለን በሚል ከፌደራልና ከዞኑ የተውጣጡ የዎላይታ ተወላጆች ወደ ስፍራው ከተጓዙ በኋላ ወጣቶችንና ነጋዴዎችን በተናጠል ለማድረግ ያደረጉት ጥረት መረጃው ቀድሞ ወደ አካባቢው በመድረሱ በነዋሪዎቹ እንቢተኝነት እንዳልተሳካ ጉዳይን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የዎላይታ ተወላጆች ገልጸዋል።
” በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙት የዞኑ አመራሮች ያቀረቡት የግለሰብ ጥያቄ ሳይሆን የሁላችንም ነው” ሲሉ ምላሽ የሰጡት የዎላይታ ተወላጆች “በቅድሚያ ተወካዮቻችንና የዞኑ አመራሮች ሊፈቱ ይገባል። ጥያቄው ለእስር የሚያበቃም ከሆነ ሁላችንም አብረን ልንታሰር ይገባል” ማለታቸውን የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች አረጋግጠዋል።
የሕዝቡ ወጥ የሆነ አቋም ያስደነገጣቸው የመፍትኄ አፈላላጊ ቡድንም በስተመጨረሻ ፤ በወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱ የዞኑ አመራሮች ክሳቸው እንዲቋረጥ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ እናቀርባለን የሚል ቃል ለነዋሪዎቹ ገብተው መመለሳቸው ታውቋል።
ከክልልነት ጥያቄ በተያያዘ ከሳምንታት በፊት በወላይታ ዞን በተቀሰቀሰው አመፅና ተቃውሞ ላይ ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለወደመው ንብረት ተጠያቂ ናችሁ በሚል 21 የዞኑ አመራሮችና የሕዝብ ተወካዮች በእስር ላይ መሆናቸው አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY