በባሌ ዞን በተመረዘ የጉድጓድ ውሃ ሰዎችና እንስሳት ለከፋ ጉዳት ተዳረጉ

በባሌ ዞን በተመረዘ የጉድጓድ ውሃ ሰዎችና እንስሳት ለከፋ ጉዳት ተዳረጉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በምስራቅ ባሌ ዞን የተመረዘ ውሃ የጠጡ ከ100 በላይ ፍየሎች ሲሞቱ ስምንት ሰዎች ደግሞ ታመው ሕክምና እርዳታ ማግኘታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

በዞኑ ራይቱ ወረዳ በሃረዱቤ ገበሬ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ከ500 በላይ የሚሆኑ ፍየሎች የተመረዘ ውሃ በመጠጣታቸው ከመካከላቸው 102 ሲሞቱ አራት መቶዎቹ መትረፋቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ አስረድተዋል።
አደጋው በደረሰበት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኡመር አብዱላሂ አካባቢው በረሃማ በመሆኑ ለሰዉም ሆነ ለእንስሳት ለመጠጥ የሚውለው ውሃ ከጉድጓድ የሚቀዳ መሆኑን ጠቁመው፤ ውሃውን ከጥልቅ ጉድጓድ በገመድ እየጎተቱ በማውጣት እንደሚጠቀሙ ከመግለጻቸው ባሻገር፤ “ከድሮ ጀምሮም በዚህ መንገድ ነው የምንጠቀመው፤ ቅርብ ጊዜ ግን አይተን በማናውቀው መልኩ 97 ፍየሎች ውሃውን እንደጠጡ ወዲያውኑ ሞቱ” ሲሉም ተናግረዋል።
አምስቱ ፍየሎች ደግሞ የእንስሳት ህክምና ማዕከል ደርሰው የሞቱ ሲሆኑ ሌሎቹ ውሃውን እንደጠጡ ወዲያውኑ መሞታቸውን፣ ከፍየሎቹ ውጪም ከጉድጓዱ ውሃውን የጠጡ ስምንት ሰዎች ታምመው እንደነበር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በውሃው የተመረዙት ስምንት ሰዎች በአካባቢው በሚገኝ ጤና ተቋም ህክምና እርዳታ አግኝተው በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ኡመር፣ ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት ችግር ገጥሟቸው እንደማያውቅም ይፋ አድርገዋል።
 “አንደኛ መርዛማ አውሬዎች፤ እንደ እባብ ያለ ውሃ ውስጥ ገብቶ ሊሆን ይችላል፤ ሌላኛው ደግሞ ድንበር ላይ ነው የምንኖረው፤ በዚህ ውሃ ላይ ደግሞ በተደጋጋሚ ግጭቶች አሉ፤ ምናልባት ሰዎች መርዘውት ሊሆን ይችላል” ሲሉም የአካባቢው ነዋሪዎች የአደጋውን ምክንያት በተመለከተ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

LEAVE A REPLY