ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በማረሚያ ቤትና በመደበኛ ስምሪት ላይ የሚገኙ ፖሊሶች ራሳቸውን ፣ እንዲሁም በህግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎችንና ኅብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ መጠበቅ አለባቸው ተባለ።
ሕግ የሚያስከብሩ ፖሊሶች በአጥፊዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ቢኖራቸውም፤ ለዓለም ዐቀፍ ሕጎች የመገዛት ግዴታ እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በተለይ እንደ ኮሮና ቫይረስ ያለ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ጊዜ ፖሊስ ሥልጣኑን እና ወረርሽኙን እንዴት አጣጥሞ መሄድ እንደሚችል ማስተዋል አለበት ሲል ዓለም ዐቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታውቋል።
ኮሚቴው ለሚመለከታቸው ባለሙያዎች ሥልጠና ሲሰጥ እንዳስተዋልነው፤ ፖሊስ እንደ ቀድሞ ሳይሆን ከዚያ በተሻለ ለራሱ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፣ የተሻለ ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ ሊኖረው ይገባልም ተብሏል፡፡
በስልጠናው ላይ የተገኙ የፖሊስ አባላትም የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ወዲህ በቀደመው ጊዜ ለስምሪት የሚወጡ ፖሊሶች ተጋላጭነት ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ይህን መቀነስ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
ሆኖም የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት የሕብረተሰቡ ለሕግ ተገዢ ያለመሆን፣ ስለ ቫይረሱ ያለው ግንዛቤ ተመሳሳይ አለመሆን፣ እንዲሁም የባህላዊ ልምዶቻችን አለመሻሻልና የፖሊስ ቁጥር አነስተኛ መሆን ፈተና ሆነውብናል ነው ያሉት የፖሊስ አባላቱ።
ከፖሊስና ወረርሽኝን ከመከላከል ጋር በተያያዘ ሌላው ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው የማረሚያ ቤት አያያዝ እንደሆነ የሚናገረው የቀይ መስቀል ኮሚቴ፤ በተለይም የማረሚያ ቤት ጠባቂዎችና መርማሪዎች የኮሮና ቫይረስ ምልክት ላያሳይ ስለሚችል በሽታውን ወደ ቤተሰቦቻቸውና ሕብረተሰቡ ላለማዳረስ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተነግሯል።