እስክንድር ነጋን በተመለከተ ባልደራስ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ሊመሠርት ነው

እስክንድር ነጋን በተመለከተ ባልደራስ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ሊመሠርት ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በእስር ላይ የሚገኘው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዘዳንት አቶ እስክንድር ነጋን በተመለከተ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ሊመሰረት መሆኑን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ አስታወቁ።

ፓርቲው ክሱን የሚመሰርተው ከአቶ እስክንድር በተጨማሪ በፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሓላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል እና የክፍለ ከተማ አደራጅ ቀለብ (አስቴር) ስዩም ጉዳይ ጭምር እንደሆነም ተሰምቷል።
“በመጨረሻው የአቶ እስክንድር እና የአቶ ስንታየሁ የፍርድ ቤት ቀጠሮ፤ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት 15 ቀን ተሰጥቶት ነበር። ዛሬ ነሐሴ 28 ቀን 2012 ዓ. ም 17 ቀን ቢሆንም ዐቃቤ ሕግ ክስ አልመሠረተም። ስለዚህ አካልን ነጻ የማውጥት ክስ እንመሰርታለን” ያሉት  የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው፤ ዛሬ ረፋድ ላይ እስክንድር ነጋና ስንታየሁን አግኝተው ባነጋገሯቸው ወቅት በፓርቲው የሕግ ክፍል በኩል አካልን ነጻ የማውጣት ክሱ እንዲመሰረት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን እንዲሰጡና የፍርድ ሂደቱም በዝግ ችሎት እንዲካሄድ ሲወሰን እስክንድር ነጋ በሂደቱ መሳተፍ እንደማይፈልግ ገልጾ ጠበቃውንም አሰናብቶ ነበር። “በከፍተኛ ወንጀል ተከሰን ለምን ችሎቱ በዝግ ይካሄዳል? ፍርድ ቤቱ ላይ አልተማመንም” በማለቱ ከዛ በኋላ በየጊዜው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲኖር በፍቃዱ ሳይሆን ፖሊስ አስገድዶ እየወሰደው እንደሚገኝ አቶ ገለታው ተናግረዋል።
በዝግ ችሎት የምስክሮች ቃል ከተሰማ በኋላ እስካሁን ድረስ ዐቃቤ ሕግ በተሰጠው 15 ቀን ክስ ባለመመሥረቱ አካልን ነጻ የማውጣት ክስ ለመክፈት መወሰናቸውን የገለጹት የሕዝብ ግንኙነቱ ባለሙያው፤ “የፖለቲካ እስር እንደሆነ ይታወቃል፤ ምስክር ተብሎ የቀረበውም አሳፋሪ ነው። ለወደፊት ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ስለሚፈራ ፓርቲውን ለማዳከም ነው። ባልደራስ ላይ ልዩ የፖለቲካ ጫና እየተደረገ ይገኛል” ብለዋል።

LEAVE A REPLY