ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ፌስ ቡክ በጎርጎሮሳውያኑ ሕዳር 3 ከሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ በፊት ባሉት ሠባት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ማስታወቂያዎችን አላስተናግድም አለ።
ይሁን እንጂ ድርጅቱ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ዒላማ ያደረጉና አሁን ያሉ ማስታወቂያዎች እንዲሄዱ የሚፈቅድ መሆኑን ገልጿል።
የፌስቡክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ በመልእክቱ ”ከምርጫው ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ክፍፍሎች ምከንያት አለመረጋጋት እንዳይፈጠር ስጋት አለኝ” ሲል ገልጿል።
የምርጫው ውጤት ይፋዊ በሆነ መንገድ ከመገለጹ በፊት ማሸነፋቸውን በፌስቡክ የሚገልጹ እጩዎችንም ቢሆን በቅርበት እንደሚከታተሉና እንደሚቆጣጠሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አያይዘው አስታውቀዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያው ፌስቡክ በቅርብ ዓመታት አነስተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች ብቻ ስለሚመለከቷቸው በማለት ፖለቲካዊ ማስታወቂያዎችን ዝም ብሎ ለቋል የሚል ክስ ሲቀርብበት መቆየቱም አይዘነጋም።
እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው ሐሰተኛ መረጃዎችን ያለምንም ጠያቂ እንዲያሰራጩ እድል ይፈጥራል የሚለው የሞዚላ ፋውንዴሽን፤ ፌስቡክ ፖለቲከኞች በማስታወቂያቸው ውስጥ የሚናገሩት ነገር እውነት ይሁን ውሸት አይጣራም ነበር ማለቱ ነገሮችን አወዛጋቢ እንዳደረገውም ገልጿል።
ከፍተኛ ተከታይ ያለው ፌስ ቡክ ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰሜን ካሮሊና መራጮች ሁለት ጊዜ እንዲመርጡ መልዕክታቸውን ያስተላለፉበት ተንቀሳቃሽ ምስል ሕገወጥ በመሆኑ አጠፋዋለሁ ሲልም አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ በሚያደርጓቸው ንግግሮች ምርጫው ሊጭበረበር እንደሚችል ሲገልፁ ቢቆዮም፤ ነገር ግን ምንም አይነት ማጭበርበር ሊኖር ስለመቻሉ ተቀባይነት ያለው ማስረጃ እስካሁን አልተገኘም።