ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የክረምቱ ዝናብ አሁንም የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ዳግመኛ አስጠነቀቀ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አየር ትንበያ ዋና ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ጫሊ ደበሌ ፤ የክረምት ዝናብ በቀጣዮች ቀናትም የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
አሁን ላይ ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚያሳዮት የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በአርሲና በምስራቅ ሸዋ ዞኖች ዘጠኝ ወረዳዎችና 42 ቀበሌዎች ወደ 20 ሺኅ የሚጠጉ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተሰምቷል።
በተመሳሳይ በአፋር ክልል በሚገኙ 14 ወረዳዎች ደግሞ በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ ከ120 ሺኅ በላይ ሰዎች በጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የክልሉ የአደጋ መከላከል ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ቢሮ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ እስከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ የጣለው ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት 170 ሺህኅ ያህል ነዋሪዎች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ 130 ሺኅ ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር ተናግረዋል።
የኦሮሚያ የአደጋ ስጋት ኮሚሽነር አባድር አብዳ ፤ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ሰዎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉንና ንብረት ማውደሙን ጠቁመው፤ ” የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በመፍሰሱ በአርሲና በምስራቅ ዞኖች ዘጠኝ ወረዳዎች 42 ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ከ19 ሺኅ 900 በላይ ሰዎች ጎድቷል” ሲሉ የአደጋውን ጥልቀት ለማሳየት ሞክረዋል።
ጉዳዮን አስመልክቶ የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ሊታሰብበት ይገባል ሲል ባወጣው መግለጫ በቀጣይ ቀናትም ከዝናቡ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጉዳት በተለያዮ ቦታዎች ሊደርስ ስለሚችል ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ተብሏል።