ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በትግራይ ክልል ሊካሄድ የታሰበውን ምርጫ ለማስቆም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ እንደ ጦርነት አዋጅ እቆጥረዋለሁ ሲል ህወሓት መግለጫ አወጣ።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነገ ቅዳሜ የሚካሄድ አስቸኳይ ስብሰባን መጥራቱን ተከትሎ ነው።
ኢትዮጵያ ነገ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለቅዳሜ የጠራው አስቸኳይ ጳጉሜ አራት ቀን በትግራይ ስለሚካሄደው ክልላዊ ምርጫ አስመልክቶ ውሳኔ ለማሳለፍ መሆኑን ታማኝ ምንጮቹን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለአባላቱ ባስተላለፈው ጥሪ ላይ 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ አስቻኳይ ስብሰባ ነሐሴ 30/2ዐ12 ዓ.ም እንደሚካሄድ ከማሳወቅ ውጪ በምን አጀንዳ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ እስካሁን የገለጸው ነገር ባይኖርም፤ የትግራይ ክልል ሥራ አስፈጻሚ በክልሉ በሚካሄድ ምርጫ ላይ የሚሰጥን ውሳኔ እንደማይቀበለው ከወዲሁ ይፋ አድርጓል።
ህወሓት የፌደሬሽን ምክር ቤት የጠራውን አስቸኳይ ስብሰባ ያልተለመደና አጀንዳውም የማይታወቅ ሲል ቢጠቅሰውም ፤ በትግራይ የሚካሄደው ምርጫን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ሊተላለፉ እንደሚችሉ ባስቀመጣቸው ሀሳቦች አመልክቷል።
ነሃሴ 27 ቀን 2012 ዓ.ም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ጉባዔ ለማካሄድ በሚያስብበት ወቅት አጀንዳውን ለአባላቱ መግለጽ እንደሚጠበቅበት አስረድቶ፣ በተደጋጋሚ ስለአጀንዳው መጠየቁንም አስታውቆ፤ አጀንዳውን በማያውቁት ጉባዔ እንዲሳተፉ የተጋበዙ ቢሆንም አስቀድሞ አጀንዳው የማይገለፅላቸው ከሆነ ለመሳተፍ እንደማይችሉ አረጋግጧል።
“ምርጫውን ለማስቆም ወይም ለማደናቀፍ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወስደው ማናቸውም ውሳኔ እንደጦርነት አዋጅ ይቆጠራል” ያለው የህወሓት መግለጫ በዚህ ምክንያት ለሚፈጠር ችግር ተጠያቂው የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባልም ሲል አሳስቧል።
ምርጫውን ለማስቆም የሚተላለፍ ውሳኔ ተቀባይነት የለውም የሚለው የህወሓት/ ትግራይ ክልላዊ መንግሥት “ሕዝቡ በምርጫ የሚያስተዳድረውን አካል እንዲመርጥ ሊበረታታ ይገባዋል እንጂ ይህን ሂደት ለማስቆም የሚደረግ ጥረት ፀረ ዲሞክራሲያዊ ነው” ብሏል።