ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ህወሓት ህገ መንግሥቱንና የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በሚጻረር መልኩ ከሦስት ቀናት በኋላ ሊያካሂድ ያሰበውን የትግራይ ክልል ምርጫ አስመልክቶ ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጠው የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ አሳለፈ።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙ ከሕገ መንግስቱ የሚቃረን መሆኑን የገለጸው የፌደሬሽን ምክር ቤት ፤ የክልሉ ም/ቤት ያሳለፏቸው ውሳኔዎች እና የፈፀሟቸው ተግባራት ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(1) መሰረት እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው ሲልም መረር ያለ ውሳኔ አሳልፏል።
“የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዙር የፓርላማ ዘመን 5ኛ አመት 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ወደ ጎን በመተው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ያወጣው የምርጫ አዋጅ ቁጥር 351/2012 እና አዋጁን መሰረት አድርጎ ያቋቋመው የምርጫ ኮሚሽን፣ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እና የፈፃማቸው ተግባራት የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔ እንዲሰጥበት በሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ተጣርቶ ለመጨረሻ ውሳኔ ለምክር ቤቱ በሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች በኩል በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡” ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል ም/ቤት የወሰደው እርምጃ በሙሉ ህግን የሚጻረር በመሆኑ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ ክብር አለኝ የፌደሬሽን ምክር ቤት ህገወጥ አካላት በሚፈፅሙት ድርጊት ምክንያት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም ብሎ የሚያምን በመሆኑ በቀጣይም ችግሮችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክር ቤቱ ከመግባባት ላይ ደርሷል ሲል አስታውቋል።