ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ኪት ከአንድ ወር በኋላ ማምረት እንደሚጀመር የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ኮሮና ቫይረስን የመመርመር አቅምን ከፍ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከአንድ ወር በኋላ ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር የመመርመሪያ ኪት ለማምረት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ሓላፊዋ፤ ለእዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ድጋፉን ከምታደርገው የቻይና መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ እየመከሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
” የመመርመሪያ ኪቱን በሃገር ውስጥ ማምረት ሲጀመር ከውጭ የሚገባውን ኪት ሙሉ በሙሉ ያስቀራል ያሉት ዶክተር ደረጀ፣ በቀጣይም ምርቱ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት እንደሚዳረስ ከመናገራቸው ባሻገር፤ ከእዚህ በተጨማሪ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የመመርመር አቅም በእጅጉ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢንፌክሽን መከላከያ ግብዓቶች በኢትዮጵያ በስፋት መመረት የተጀመሩ ሲሆን፤ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሶችን ወደ ውጭ ሃገራት እየላከ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።
በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሚገኙ ኩባንያዎች እነዚህን ቁሶች በማምረት ቀዳሚ መሆናቸውን ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታው ፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 52 የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላት እንደሚገኙና በእነዚህም በቀን ከ20 ሺኅ በላይ ናሙናዎችን መመርመር መቻሉን ይፋ አድርገዋል።