ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የታከለ ኡማ አስተዳደር በአዲስ አበባ የፈጸመውን ብሔርተኝነትን የተመረኮዘ የመሬት ወረረራና ህገ ወጥ የኮንዶሚኒየም እደላ በተጨባጭ ማስረጃ ያረጋገጠው የኢዜማ ከፍተኛ አመራሮች የዐይን ብሌናቸውን ከህልፈታቸው በኋላ ለመለገስ ቃል ገቡ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፓርቲ (ኢዜማ) ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች በኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት ከህልፈታቸው በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ የሚያስችላቸውን የዐይን ባንኩ የቃልኪዳን ሰነድ ላይ ፊርማቸውን አስቀምጠዋል።
አባላቱ ተቋሙ ድረስ መጥተው መልካሙን ነገር ለማድረግ ቃል በመግባታቸው ምስጋናቸውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ የዐይን ባንክ ዳይሬክተር ወ/ሮ ለምለም አየለ፤ ሌሎች የኅብረተሰብ አካለትም ከህልፈታቸው በኋላ ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንደገቡ ይፋዊ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው ” ከስጦታዎች ሁሉ የላቀውን የብርሃን ስጦታ ከህልፈታችን በኋላ ለመልገስ ቃል በመግባታችን ኩራት ይሰማናል” ከማለታቸው ባሻገር፣ በቀጣይም ሌሎች ማኅበረስቦችን በማንቃት ቃል እንዲገቡ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የዐይን ባንክ እስካሁን ለ2 ሺኅ 465 ወገኖች የብሌን ንቅለ ተከላ ተከናውኖላቸው ብርሃናቸው እንዲመለስ ማድረጉን የኢዜማ አመራሮች በጎ ተግባር በፈጸሙበት ወቅት ገልጸዋል።