ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል በወያኔ ዘመን ለዓመታት ታስረውበት ወደነበረው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተዘዋወሩ።
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ ላይ ዐቃቤ ሕግ የፀረ ሽብር አዋጅን በመተላለፍ ክስ መስርቶበታል። በፖለቲከኛውና ጋዜጠኛው እስክንድር ነጋ ላይ የቀረቡት ክሶች ኃይልን በመጠቀም መንግሥትን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራን የሚጠቅሱ መሆናቸውም አይዘነጋም።
ጳጉሜ 5/2012 ዓ.ም በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ላይ አቶ እስክንድር ላይ ክስ በመመስረቱ፤ ፍርድ ቤቱ ክስ የቀረበባቸው እነ አስክንድር ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ማዘዙን ተከትሎ፤ በትናንትናው ዕለት መስከረም 06/2013 ዓ.ም ከነበሩበት የፌደራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት በተለምዶ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወደ ሚባለው መዛወራቸውን ኢትዮጵያ ነገ ዛሬ ከቅርብ የቤተሰብ አባላት ማረጋገጥ ችሏል።
እስክንድር ነጋ ከዚህ ቀደም በቃሊቲ ከስድስት ዓመታት በላይ በታሰሩበት ስፍራ እና ክፍል አሁን ዳግም እንደታሰረ ለማወቅ ችለናል።