እስክንድር ነጋና ስንታየሁ ቸኮል ” ታከለ ኡማን ስታስጨንቁ ነበር ” የሚል ውንጀላ...

እስክንድር ነጋና ስንታየሁ ቸኮል ” ታከለ ኡማን ስታስጨንቁ ነበር ” የሚል ውንጀላ ቀረበባቸው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ዛሬ እስክንድር ነጋን ጭምሮ በክስ መዝገቡ ላይ የሚገኙ 4 ሰዎች በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበው ክሳቸው ተነበበላቸው።

በችሎቱ ክሱ ከተነበበና አስተያየት ከተሰማ በኋላ በጠበቆች በኩል የዋስትና ጥያቄ ቀርቦ ነበር። የተከሳሽ ጠበቃ “የቀረበባቸው ክስ ዋስትና የሚያስከለክላቸው አይደለም” በሚል ጥያቄውን ቢያቀርቡም፤ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ” የዋስትና መብት ሊከበርላቸው አይገባም፤ እነአቶ እስክንድር ቢፈቱ ለአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ትልቅ አደጋ ይፈጠራል” በሚል ተከራክሯል።
እነ እስክንድር ይህንን የዐቃቤ ሕግ መከራከሪያ በመቃወም የተከራከሩ ሲሆን፤ እስክንድር ነጋ፤ ፓርቲያቸው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የተሻለ አማራጭ ያለው ፓርቲ መሆኑን በመጥቀስ ፣ በቀጣዩ ምርጫ የእነርሱ መወዳደር ለአገሪቱ ዲሞክራሲ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ለችሎቱ ከመጠቆሙ ባሻገር፤ ምርጫው በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት እንዲኖረው የእርሱ በምርጫ መሳተፍ ወሳኝ መሆኑንም ገልጿል።
በዐቃቤ ሕግ በኩል “አቶ ታከለ ኡማን አስጨንቃችሁታል” ለሚለው ውንጀላ ከንቲባውን ማስጨነቃቸው ተገቢ እንደነበር የገለጸው ስንታየሁ ቸኮል፤ የሠራነው ሥራ ተገቢና የታፈነ ሕዝብ ድምፅን ማስተጋባት ነበር ሲል ተከራክሯል።
ቀሪዎቹ ሁለት ተከሳሾችም የቀረበው ክስ ተገቢ አይደለም በማለት የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው የተከራከሩ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም የሁለቱንም ወገን መከራከሪያ ከሰማ በኋላ ብይን ለመስጠት ለማክሰኞ መስከረም 12/2013 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።

LEAVE A REPLY