ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ኮሮና ቫይረስን ሊያክሙ ይችላሉ ተብለው በቀረቡ አምስት መድኃኒቶች ላይ ምርምር እየተደረገ መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ተቋም የባህልና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር አስታወቀ።
የተቋሙ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ወርቁ ገመቹ ፤ ከባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማኅበር በኩል ለኮቪድ-19 ይሆናሉ የተባሉ ከ50 በላይ መድኃኒቶች ለምርምር ማዕከሉ መቅረቡን ገልጸዋል።
ነገር ግን በአቅምና በሰው ኃይል ውስንነት ምክንያት ከእነዚህ መካከል 5 ያህሉን መርጠው መመልከታቸውንና ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት ሓላፊው፤ ባህላዊ መድኃኒቶቹ በጭስ መልክ የሚታጠን፣ በሻይ መልክ የሚጠጣ፣ በቅባት መልክ የቀረበ፣ በምግብ መልክ የሚወሰዱ እንደመሆናቸው ምርምር እንዲደረግባቸው መቅረባቸውንም አብራርተዋል።
ከቀረቡት መድኃኒቶች መካከል በጭስ መልክ የቀረበውን በላብራቶሪ ደኅንነቱን ለማጥናት ስለማይቻል ተቋሙ እንዳልተቀበለው የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤
የተመረጡት አምስቱ ባህላዊ መድኃኒቶች ግን በሻይ መልክ፣ በምግብ መልክ፣ በቅባት መልክ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው የጥናት ሂደት ለመድኃኒቶቹ ጥቅም ላይ የዋሉትን የእፅዋት አይነቶችና ዝርያቸውን መለየታቸውን፣ ተያያዥ የጽሑፍ ዳሰሳ በማድረግ መረጃው ተሰንዶ ወደ ቀጣይ ሂደት ለመሻገር ዝግጅት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።
መድኃኒቶቹ ከአምስት ሰዎች የመጡ ቢሆንም ከ30 በላይ እፅዋት የተካተቱበት በመሆኑ፤ ለ30ዎቹ የእፅዋት ዓይነቶችም የተያያዥ ጽሑፍ ዳሰሳ መሠራቱ ታውቋል።
በተደረገው ዳሰሳ ወይም ጥናት የእፅዋቱን ምንነት፣ ተመሳሳይ ስም ያላቸውን የመለየት፣ አካባቢያዊ ስም መኖር አለመኖሩን የማጥራት፣ በሃገር ዐቀፍም ሆነ በዓለም ዙሪያም የእፅዋቶቹ መገኛ የት እንደሆነና ለምን እንደሚጠቀሙባቸው? የማጥናትና የመለየት ሥራ መከናወኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እፅዋቶቹ በውስጣቸው ምን ዓይነት ኬሚካሎች ይዘዋል? የሚለውን በተመለከተም በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት ተካሂዶባቸው መሆን አለመሆኑ፤ እንዲሁም ደኅንነታቸውንና የጎንዮሽ ጉዳት ካላቸው መለየትና ሰው ላይ ተሞክሮ እንደሆነ በዳሰሳቸው የተመለከተ ቢሆንም፤ ነገር ግን እስካሁን ሰው ላይ የተሞከረ አለማግኘታቸውን የተቋሙ ሓላፊ አስታውቀዋል።