ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ አየር መንገድ አትራፊ ሆነዋል ከተባሉ ሦስት የአለማችን አየር መንገዶች አንዱ ለመሆን መቻሉ ተሰማ።
የኮቪድ-19 በሽታ የዓለምን ኢኮኖሚ ባቃወሰበት ወቅት ሦስት አየር መንገዶች በትርፋማነታቸው ቀዳሚ ለመሆን መብቃታቸው በመነገር ላይ ነው።
ፎርብስ በድረ-ገፁ ባሰፈረው የትርፋማ አየር መንገዶች ዝርዝር መሠረት የኮሪያ፣ የኤስያና የኢትዮጵያ አየር መንገዶች ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ቅደም ተከተል ይዘዋል።
የተጠቀሱት አየር መንገዶች ሳይከስሩ፣ ቢያንስ ወጪያቸውን በመሸፈን ትርፋማ ሊሆኑ የቻሉት በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ለውጥ ማድረጋቸው በመሆኑ እንደሆነ ዝርዝር የጥናት ውጤቱ ይፋ አድርጓል።
የሃገራቱ አየር መንገዶች የኮሮና ወረርሺኝ ከተከሰተ ወዲህ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ወደ እቃ ጫኝ ትራንፖርት መቀየራቸው ለትርፋማነታቸው ዋንኛ ምክንያት እንደሆነ ፎርብስን ዋቢ ያደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድኅረ ገጽም መረጃው ትክክል እንደሆነም አረጋግጧል።