ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኦሮሚያ ክልል በቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና የክልሉ ፕሬዝዳንት በነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ ለተመሰረተው ዲቦራ ፋውንዴሽን 10 ሚሊዮን ብር እለግሳለሁ አለ።
የክልሉ መንግስት ገንዘቡን ለመስጠት ቃል የገባው ፋውንዴሽኑ በለገጣፎ ለሚያሠራው ትምህርት ቤት፣ የጤና አገልግሎት መስጫ እና ማሰልጠኛ ማዕከል እንደሆነም ታውቋል።
ዲቦራ ፋውንዴሽን ዳውንሲንድረም ተብሎ በሚታወቀው የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት የተጠቁ ህጻናትን ለመደገፍ በሐምሌ 2011 ዓ.ም. የተቋቋመና በአባዱላ ገመዳ አራተኛ ልጅ ስም መጠሪያውን ያደረገ የበጎ አድራጎት ተቋም ነው።
በቅዳሜ ምሽቱ የፋውንዴሽኑ የማሰልጠኛ ማዕከል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከመንግሥት እና ከግል ተቋማት ያልተጠበቁ ልገሳዎች በዚያው በመድረኩ ሲሰጡ ነበር። ከመንግሥት በኩል ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው የኦሮሚያ ክልል ሲሆን፣ ለማሰልጠኛው ግንባታ የክልሉ መንግሥት ለመስጠት ቃል ከገባው 10 ሚሊዮን ብር በተጨማሪ የክልሉ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የመዋዕለ ህጻናት ግንባታውን ራሱ ለማከናወን እንደወሰነም ገልጿል።
የኦሮሚያ ክልሉ የትምህርት ቢሮ በበኩሉ ሽያጩ ለፋውንዴሽኑ እንዲውል በሚል በአቶ አባዱላ የተጻፉ 10 ሺህ መጽሐፍትን ለመግዛት ቃል የገባ ሲሆን፤ መጽሐፍቱ በክልሉ ባሉ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፋፈሉ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል። ከትምህርት ቢሮ በተጨማሪ የተለያዩ የግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች ወደ አራት ሺኅ ገደማ መጽሐፍት ለመግዛት ቃል ገብተዋል።