ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በመተከል ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ተሳተፈዋል የተባሉ 358 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።
በቅርቡ በመተከል ዞን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የክልሉና የፌዴራል መንግሥት በትኩረት እየሠሩ መሆናቸውን የተናገሩት የቢሮው ሓላፊ አቶ አበራ ያበታ፤ ከሰሞኑ በመተከል ዞን ቡለን እና ወምበራ ወረዳ አንዳንድ ቀበሌዎች ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ አየተሠራ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራ የተለያዩ ተሳትፎዎችን አድርገዋል የተባሉ ተጨማሪ 30 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች ተሳትፎ የነበራቸው 328 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበርና ሰሞኑን በሁለቱ ወረዳዎች እየተሠራ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራ ተጨማሪ 30 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
በጠቅላላው እስካሁን በተካሄደው የህግ ማስከበር ሥራ ለችግሩ መፈጠረና መባባስ የተለያዩ ተሳትፎ የነበራቸው 358 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ የፀጥታ ሓላፊው ተናግረዋል።