ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዐሥር ዓመታት ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ የመሆን ግቧ አካል የሆኑ ሁለት የመዝናኛ (ሪዞርት) ከተማዎችን ልትገነባ ነው።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ የቱሪዝም እቅድ ዘርፍ መሪ አቶ አህመድ መሐመድ ከመዝናኛ ከተሞቹ አንዱ የሚገነባው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እንደሆነ ጠቁመው፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ 70 ገደማ ሰው ሠራሽ ደሴቶች እንደሚኖረውና በሀገሪቱ ዋነኛው የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ሁለተኛው የመዝናኛ ከተማ የሚገነባበት ቦታ የአዋጪነት ጥናት ከተካሄደ በኋላ እንደሚወሰን የጠቆሙት ሓላፊው፤ የመዝናኛ ከተማ ግንባታ የሚከናወነው የግሉ ሴክተርን ጨምሮ በብዙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ነው ብለዋል።
ሪዞርቶች በግል ባለሀብቶች ይገነባሉ ያሉት አቶ አህመድ፤ የመዝናኛ ከተማዎቹ ሀገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ ከፍ እንደሚያደርግ ከመጠቆማቸው ባሻገር፤ ኢትዮጵያ በ2022 የቱሪስቶችን ቁጥር 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለማድረስና ከቱሪዝም ዘርፍ ብቻ የሚገኘውን ገቢ 23 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እቅድ እንድትነድፍ አስስችሏል ሲሉ አብራርተዋል።
በቀጣዮቹ ዐሥር ዓመታት ውስጥ በነባር 40 መዳረሻዎች ላይ እሴት በመጨመር በመላ ሃገሪቱ 59 አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ለማልማት እቅድ በሃገር ደረጃ መያዙም ተሰምቷል።