ኢትዮጵያ ነገ ዜና|| በቻይና የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ መስጠት ሊጀምር መሆኑን ገለጸ።
የዩኒቨርሲቲው የአማርኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር ምስረታ ሥነ ሥርዓት ዛሬ በቤጂንግ እየተካሄደ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ይፋ አድርጓል።
ትምህርቱ የሚሰጠው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አማካኝነት ሲሆን፤ በስምምነቱ መሠረት የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ይሰጣል።
በዚሁ መሰረት የአማርኛ ቋንቋ በቻይና የትምህርት ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ይሰጣል ነው የተባለው። የምስረታ መርሃ ግብሩ ላይ የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ጂያ ውንጂንና በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካይ አቶ ሳሙኤል ፍጹምብርሃን መገኘታቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ በ1941 የተመሰረተ ሲሆን በቻይና በውጭ ቋንቋዎች ጥናት ላይ ትኩረት አድርጎ የተቋቋመ የመጀመሪያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው። ዩኒቨርሲቲው በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ የውጭ አገራት ዜጎችን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ከ8 ሺኅ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።