የደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ሳይጓደል እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስታወቀች

የደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ሳይጓደል እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስታወቀች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና||  የ2013 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ሙሉ ሃይማኖታዊ እሴቱና ሥርዓቱ ሳይጓደል እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤቸ ክርስቲያን አስታወቀች።

የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ዐቢይ ኮሚቴ አባል የሆኑት መጋቤ ሰላም ሰሎሞን ቶልቻ፤ በአዲስ አበባ በርካታ ምዕመናን ተገኝተው የሚያከብሩበት የመስቀል አደባባይ በግንባታ ላይ መሆኑ የበዓሉን ሃይማኖታዊ እሴቱና ሥርዓቱ እንደማያጓድለው ተናግረዋል።
በዓሉን ለማክበር የሚታደሙ ምዕመናን ቁጥር በተወሰነ መልኩ መቀነሱን የጠቆሙት መጋቤ ሰላም ሰሎሞን፤ አካባቢው ግንባታ ላይ በመሆኑ እና የግንባታ ቁሳቁስ በስፍራው ላይ መኖሩ፣ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በክብረ በዓሉ ላይ በርካታ ሰዎች እንዳይገኙ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
መስከረም 16 በመስቀል አደባባይ በመገኘት በዓሉን የሚታደሙና የሚያከብሩ ሰዎች ቁጥር ከ5 ሺኅ እንደማይበልጥ የገለፁት የኮሚቴው አባል፤ የመግቢያ ባጆች ከ3 ሺኅ እስከ 5 ሺኅ እንደሚታተሙ ከመናገራቸው ባሻገር፤ ቤተክርስትያኒቱ ከፀጥታ አካል ጋር በመተባበር በበዓሉ ላይ ለሚታደሙ የክብር እንግዶች እንዲሁም ምዕመናን፣ መዘምራንና ቀሳውስት ባጆችን እንደምታዘጋጅ ከወዲሁ ይፋ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና የሐዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሓላፊ የሆኑት መጋቢ ሰላም ሰሎሞን፤ የ2013 ዓ.ም የመስቀል በዓልን ለማክበር ካሉት ሦስት ተግዳሮቶች መሀል ቀዳሚው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ ምክንያት በዓሉን ምዕመናኑ በነቂስ ወጥቶ አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ማክበር እንደማይችሉ አብራርተዋል።
ሁለተኛው የፀጥታ ጉዳይ ሲሆን ፣ የመንግሥት የፀጥታ አካል በዓሉ ያለ ችግር እንዲከበር ከቤተክርስቲያኒቱ የበዓል አከባበር ኮሚቴ ጋር በጥምረት እንደሚሠራ ተጠቁሟል።
የመስቀል አደባባይ በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑ በሦስተኛ ደረጃ እንደሚቀመጥ ያስታወሱት የኮሚቴው አባል፤  የበዓሉ ታዳሚያን ቁጥር ይቀንሳል እንጂ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ሳይጓደል ይከበራል ብለዋል።

LEAVE A REPLY