ኢትዮጵያ ነገ ዜና|| የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትናንት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የስፖርት ኮሚሽን ዛሬ መግለጫ ሰጠ።
ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ አስፈላጊው የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች እና ጥንቃቄዎች ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ የገለጸው የስፖርት ፌዴሬሽን፤ በተለይም ስልጠናዎች እና ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት ከማዘውተሪያ ዝግጅት፣ የሰው ሀይል ቁጥርን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የመከላከያ ግብዓቶች መሟላታቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ አሳስቧል።
የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ፤ ይህን የሚከታተል ብሔራዊ ኮሚቴ እንደሚቋቋም እና ስፖርታዊ ውድድሮችም ለጊዜው በዝግ ስታዲየም እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።
በጊዜ ሂደት ወረርሽኙ ከቀነሰ የተወሰነ ተመልካች እንዲገባ ይደረጋልም ያሉት ኮሚሽነር ዱቤ ጅሎ፤ በማኅበራት በኩል ለማገገሚያ የተጠየቀውን በጀት በተመለከተ ኮሚሽኑ ለመንግስት ጥያቄውን አቅርቦ እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ተናግረዋል።