ኢትዮጵያ ነገ ዜና|| በትግራይ ክልል የግዕዝ ቋንቋን በመደበኛ የትምህርት መርሃ ግብር ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ቋንቋዎች አካዳሚና ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የትግራይ ቋንቋዎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ተክሌ ፤ አዲሱ ትውልድ ጽሑፎችን በማንበብ የሀገሩን ባህልና ቋንቋ እንዲሁም ታሪክና ማንነት ጠንቅቆ እንዲያውቅ ለማብራራት የቋንቋውን ትምህርት መስጠት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በግዕዝ ቋንቋ የተጻፉ በሺኅዎች የሚቆጠሩ ጥንታዊ የብራና መጽሐፍት ይገኛሉ። ዳይሬክተሩ በተያዘው 2013 ዓመት በክልሉ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምሀርቱን ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ይፋ አድርገዋል።
ከትግርኛ፣ ኩናምኛና ሳሆኛ ቋንቋዎች ቀጥሎ ግዕዝ አራተኛ ቋንቋ ሆኖ በክልሉ በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሓላፊነት ወስዶ እየሠራ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤
ቢሮው የመማር ማስተማር ሥራውን እንዲጀምር በክልሉ ምክር ቤት በአዋጅ መፅደቁንም አረጋግጠዋል።
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው የግዕዝ ቋንቋ ትምህርትን በክልሉ በሚገኙ ከ2 ሺኅ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለማስጀመር የመምህራንና የመማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝና ከ6 ወራት በኋላ ትምሀርቱን ለመጀመር እቅድ መያዙንም አስታውቀዋል።
የግዕዝ ቋንቋ በትምህርትነት መሰጠት በየአብያተ-ክርስትያናትና ገዳማት ውስጥ የሚገኙና በግዕዝ ቋንቋ ተጽፈው የታተሙ ጥንታዊና ታሪካዊ መጻሕፍትን በቀላሉ አንብቦ ለመረዳት አስተዋፅዖ እንዳለው እየተነገረ ይገኛል።