ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዛሬ የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የሕገ መንግሥት እና ፀረ ሽብር ጉዳዮች ችሎት፤ እስክንድር ነጋን ጨምሮ የአራት ተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ተሰማ።
በዚህ የክስ መዝገብ አምስተኛ ተከሳሽ የሆኑት ጌትነት በቀለ በ30 ሺኅ ብር ዋስ በውጭ ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ መወሰኑ ታውቋል።
እስክንድር ነጋን ጨምሮ የ7 ተከሳሾች የዋስትና መብት ላይ በቀረበው ክርክር ውሳኔ ለመስጠት፣ እንዲሁም ክሱ በግልጽ አልቀረበም በሚል ዐቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን በችሎት የተገኘው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ አስታውቋል።
ዛሬ በዋለው ችሎትም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፍርድ ቤቱ በታዘዘው መሰረት ክሱን አሻሽሎ ማቅረቡን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።
በዚህም መሰረት አቃቤ ሕግ ግምቱ 187 ሚሊዮን 358 ሺህ 459 ብር ንብረት በመውደም… ዝቅተኛው 10 ዓመት ከፍተኛው 20 ዓመት ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ …” በማለት ሌላ ተጨማሪ ውንጀላ በመጨመር ክሱን አክብድዋል። ፍ/ቤቱም ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ ዋስትና ስለሚያስከለክል ጉዳያቸውን በእስር ቤት ሆነው እንዲከታተሉ በማለት ለጥቅምት 12/2013 ዓም ቀጠሮ ስጥቷል።
አቶ እስክንድር ለፍ/ቤቱ “ጊዜው የምርጫ ስለሆነ በምርጫ መሳተፍ እንፈልጋለን። ጉዳያችን ረጅም ጊዜ ሳይፈጅ በአጭሩ እንዲያልቅልን፣ ከዚህ ልቦለድ ክስ ነፃ እንደምንወጣ ጥርጥር የለኝም። የሚጠብቀን ህዝብ አለ፣ በሕዝብ መመዘን እንፈልጋለን” በማለት ተናግራል።