ሀብታቸውን ያላሳወቁ የክ/ከተማና የወረዳ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት እንዲያስመዘግቡ ሊደረግ ነው

ሀብታቸውን ያላሳወቁ የክ/ከተማና የወረዳ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት እንዲያስመዘግቡ ሊደረግ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ይደረጋል ተባለ።
የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከዐስሩም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ አመራሮች ጋር በሀብት ምዝገባ ዙሪያ ባደረገው ውይይት ላይ፤ በተቀመጠው መደበኛ የምዝገባ ጊዜ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮች በገንዘብ ቅጣት በ5 ቀናት ውስጥ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የጊዜ ገደብ መቀመጡን ለማወቅ ተችሏል።
 ከዐሥሩ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚዎች መካከል በጊዜ ገደቡ ሀብታቸውን ያስመዘገቡት የቦሌ፣ የአራዳና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ብቻ መሆናቸዉን የጠቆሙት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ፤ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ከመስከረም 18 እስከ 22/2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በተሻሻለው የሃብት ማሳወቅ እና ምዝገባ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1/2013 መሠረት ለኮሚሽኑ የአንድ ሺህ ብር ቅጣት በመክፈል ሀብታቸውን እንዲያሳውቁ ይደረጋል ብለዋል።
ሆኖም በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሀብታቸውን በማስመዝገብ ግዴታቸውን በማይወጡ አመራሮች ላይ፤ ኮሚሽኑ በሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ ጉዳዩን አግባብነት ላለው የምርመራ አካል እንደሚያስተላልፍ ተገልጿል።

LEAVE A REPLY