ኢትዮጵያ ነገ ዜና || እየተገነባ ባለው የህዳሴ ግድብ ላይ ሊያጋጥም የሚችል የትኛውንም የጠላት እንቅስቃሴ ማስቀረት የሚያስችል የተሟላ ዝግጁነት እንዳደረገ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄነራል ይልማ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ አየር ሃይል አሁን ያለበትን ወቅታዊ ብቃትና ዝግጁነት በማስመልከት ሲናገሩ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከየትኛውም ጊዜ በላቀ መልኩ ብቃት ባላቸው አባላትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደራጅቷል ብለዋል።
ቀደም ሲል የአጭር ጊዜ በረራ ብቻ ያደርጉ የነበሩት ተዋጊ አውሮፕላኖች አሁን ከአራት ሰዐት በላይ መብረር የሚችሉና ዲጂታል መሆናቸውን ሓላፊው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን የአየር ክልል በመጠበቅ ሂደት በአንድ ማዕከል በመሆን መቆጣጠር፣ ትእዛዝ መስጠትና ግዳጆች በፍጥነትና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲፈፀም ማድረግ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል ያሉት ሜጀር ጀነራል ይልማ ፤ ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከየትኛውም ጥቃት መጠበቅ የአየር ኃይላችን ዋነኛ ተልእኮ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በግድቡ ዙሪያ የማይቋረጥ በአየር ሃይሉ ዋነኛ ክትትልና ጥበቃ እንደሚደረግ የጠቆሙት አዛዡ፤ በዚህ ዙሪያ ማንኛውንም ትንኮሳም ይሁን የጠላት እንቅስቃሴ የመመከትና የማስቀረት አስተማማኝ ብቃት እንዳለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል አሁን ለደረሰበት ያለፈው ታሪኩ ዋነኛ መሰረቱ መሆኑን የሚናገሩት ሜጀር ጀነራል ይልማ አሁን ላይ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ በአጭር ጊዜም በብቃት ተልእኮ የመፈፀም ብቃት እንዳለው ከመጠቆማቸው ባሻገር፣ አየር ኃይሉ አሁን ላይ በአቪየሽንና በአየር መከላከያ ዘመኑ የተደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ላይ እንደሚገኝም ይፋ አድርገዋል።