የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ! ኦሪት ዘህወሀት!

የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ! ኦሪት ዘህወሀት!

የግራ አስተሳሰብ ሁሌ ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባል። ህወሀት የግራ ጁንታ መሆኑ ይታወቃል። የግራ ፖለቲካ ደግሞ ውሸት ሲደጋገም እውነት እንደሚሆን ያምናል። መስከረም 25/30 የሚደጋገመዉ ለዚህ ይመስላል። ህወሀት ከፈረሶቹ ጋር ብቅ ጥልቅ እያለ ይፎክራል። በህገ-መንግስት እና በፌዴራሊዝም ስም ያለቃቅሳል። ከመስከረም 25/30 በኋላ መንግስት ስለማይኖር” ባለአደራ መንግስት ከሰማይ ይዉረድልኝ” ይላል።
ኢትዮጵያን ወደ ሊቢያ ለመቀየር አቅዶ በሙሉ ኃይሉ ይንደፋደፋል! በእርግጥ ዋነኛ እቅዱ ሰኔ 2012 መጨረሻ ላይ ተሞክሮ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ከሽፏል! አሁን ቅዠትን እዉነት ለማድረግ በህወሀት አሻንጉሊቶች በከንቱ ደንኪራ ይመታል። ይህ በአማርኛ “የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ”ይባላል!
የህወሀት ህልም ሩቅ ኖሯል። ኢትዮጵያዊያንን ከፋፍሎ እየገዛ ለመቶ ዓመታት ኢትዮጵያን የመጋጥ ግልፅ እቅድ እንደነበረዉ ይታወቃል። በዚሁ አግባብ ለ 27 ዓመታት በኢትዮጵያዊያን ሰቆቃ ውስኪ እየተራጬ ሲንደላቀቅ ኖሯል። ያ ሁኔታ መጋቢት 2010 ላይ አክትሟል። በኢትዮጵያ ህዝብ የዘመናት ትግልና በለውጥ አመራሩ ቆራጥ ውሳኔ የህወሀት ጉልበት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተንኮታኩቷል። ነገር ግን እዉነታዉ አልዋጥ ብሎታል።
የቀን ቅዠት እዉን እየመሰለዉ አስቸግሮታል! ሁሌ ድምፅ ወያኔ ላይ ወጥቶ ” ከመስከረም በኋላ ከኔ ውጭ ሌላ የለም” ይላል። “የለም! የለም!” እያለ ግልፅና ተጨባጭ እዉነታን መሰረዝ ይፈልጋል። መቸስ ከዚህ በላይ የሚገርም በዓለም ላይ ምን ይኖራል? ህወሀት ከነሙሉ ጥርሱና ጥፍሩ በነበረበት ወቅት ታግሎት ያቃተዉን ለዉጥ ከሬሳ ሳጥን ደጃፍ ሆኖ “የለም” በማለት ብቻ ለመቀልበስ ይሞክራል!
ዘንድሮ “ሰይጣን ለተንኮሉ ቅዱሳን መፅሓፍትን ይጠቅሳል” የሚባለዉ በግልፅ መታየት ጀምሯል። ህወሀት በምክንያት የኢሬቻ 2013 ዋነኛ አቀንቃኝ ሆኖ ብቅ ብሏል። በኢሬቻ አስታኮ አዲስ አበባ ላይ ተጀምሮ አዲስ አበባ ላይ እንዲያልቅ ታቅዶ የከሸፈዉን ጦርነት ዳግም ለማወጅ ፈልጓል! ፍላጎቱን ለማሳካት ደግሞ በኦሮሞ ስም የሚነግዱ አሉላ የሚቀልባቸዉን ፈረሶች አዘጋጅቷል! በፈረሶቹ በኩል የኦሮሞ ወጣት ኢሬቻን አሳቦ በነቂስ በመዉጣት ሸገር ላይ እንዲረብሽ ይቀሰቅሳል። በዲጂታል ወያኔ ደግሞ “ኢሬቻ የሰይጠን አምልኮ ነዉ” እያለ በአማራ ስም ያሰራጫል። የኦሮሞን ህዝብ “ጋኔን” ያለዉ ህወሀት መሆኑ ግን ይታወቃል። በተጨማሪም “ኢሬቻ አዲስ አበባ ላይ መከበር የለበትም” እያለ በሌላዉ አሻንጉሊቱ በኩል የሸገር ወጣቶችን ይቀሰቅሳል። ኢሬቻ 2009-ን የዘነጋነዉ መስሎታል። ያኔ ብሾፍቱ ላይ በአንድ ቀን ብቻ ከ 700 በላይ የኢሬቻ ታዳሚ ኦሮሞዎች በወያኔ አጋዚ ገደል ውስጥ ተጥለዉ ሞቷል። በዚያ ወሳኝ ወቅት “የኦሮሞ ደም ደሜ ነዉ” ያሉትን የጎንደር ወጣቶች ታሪክ መዝግቧል። ኢሬቻን መደገፍ እና ማሞገስ ከቁርጥ ቀን ወገኖች ያምራል! ዛሬ ወያኔ በግራና በቀኝ የሚያጫውታቸዉን አሻንጉሊቶች ማን ይሰማል?
ታዲያ በመጨረሻ ምን ይሆናል? ዉሾቹ እየጮሁ ግመሉ ይጓዛል! ባቡሩ ፍጥነቱን እና አቅጣጫዉን ጠብቆ ወደፊት ይገሰግሳል። ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት በከፈሉት ውድ ዋጋ የመጣዉ ለውጥ ከመስከረም 25/30 በኋላም ተጠናክሮ ይቀጥላል! የተቋማት ግንባታ እና ብሔራዊ ውይይት መሠረት ይይዛል። በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይፈጠራል። ህወሀት ሲያበላሸዉ የነበረዉ ብሔራዊ ምርጫም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልፅ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ይከወናል። የማይኖረዉ ህወሀት እና ተፅዕኖዉ ብቻ ይሆናል። ጓድ ህወሀት ቀስ እያለ ወደ መቃብሩ ጠጋ ጠጋ ይላል! በትግራይ ላይ ጠባሳ ሳይጥል፥ ማንም ሳይነካዉ ራሱን ችሎ ይሞታታል! የትግራይ ህዝብም እንደወገኖች የነፃነትን አየር ይተነፍሳል!አሉላ ፈረሶቹን የሚቀልብበት መኖ ያጣል። በዚያዉ ጋብቻዉ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ይፈርሳል። አሻንጉሊትም አስታዋሽና አጫዋች ያጣል! የሴራና የሸር ስራ ብኩን ይሆናል። የሌብነት፣ የውሸት፣ የፅንፈኝነት እና የክፋት ዘመን ያበቃል! እዉነት እና አዉቀት መርህና መመሪያ ይሆናል! የኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እና ብልፅግና ደግሞ እየጎለበተ ይሄዳል! የኢትዮጵያ ህዝብ ወንድማማችነትን መሠረታዊ መርሁ አድርጎ በድል ላይ ድል ይጎናፀፋል! ይህ ቃል ነዉ! ቃል ይነቅላል! ቃል ይተክላል! አሜን!!

LEAVE A REPLY