ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኦሮሚያ ክልል የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ ስጋት ምክንያት ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ከቆዩ ዜጎች አብዛኞቹ ወደ ቀዬአቸው ተመልሰዋል ተባለ።
በክልሉ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ ስጋት ምክንያት በርካቶች ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸው አይዘነጋም።
ምዕራብ ሸዋ፣ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች ነዋሪዎቹ ከተፈናቀሉባቸው መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በአርሲ እና ምስራቅ ሸዋ መካከል ያሉ ሌሎች ወረዳዎችም እንዲሁ በጐርፍ ስጋት ውስጥ የቆዮ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከእነዚህ አካባቢዎች እስከ 30 ሺኅ የሚደርሱ ሰዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው እንደቆዩ የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገረመው ኦሊቃ ቀደም ሲል መናገራቸው ይታወሳል።
አሁን ከእነዚህ ተፈናቃዮች የሚበዙት ወደ ቀዬአቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ ያሉት የወንዙ የውሃ ሙላት በመቀነሱ መሆኑ ተገልጿል።
አብዛኞቹ ነዋሪዎች በማሣ ላይ የነበረ እና በጎርፉ የወደመባቸውን ሰብል መልሶ በመተካት ሥራ ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ዜና፤ የክልሉ መንግሥትም ይህን ጥረት ለማገዝ ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ነዋሪዎቹ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የተደረገው ከዚህ በኋላ የጎርፍ ስጋት የለም በሚል ነው ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ገረመው በአብዛኛው ስጋቱ እንደማይኖር ጠቁመው፣ ነገር ግን ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ አካባቢዎችም እንዳሉ አስረድተዋል።
በባሌ፣ ምዕራብ ጉጂ እና ሐረርጌም በጎርፍ ስጋት ምክንያት ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የቆዩ ዜጎች እንዳሉ የሚናገሩት ሓላፊው፤ እነዚህም አሁን ወደ ቀዬአቸው ተመልሰዋል ሲሉ ተናግረዋል።