በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴት ሕጻናት ያለ እድሜያቸው ይዳራሉ ተባለ

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴት ሕጻናት ያለ እድሜያቸው ይዳራሉ ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ያለ እድሜያቸው የሚዳሩ ሴት ልጆች ቁጥርን ከፍ እንደሚያደርግ የሕጻናት አድን ድርጅቱ ሴቭ ዘ ችልድረን ይፋ አደረገ።

ባለፉት 25 ዓመታት ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የተደረገውን ጥረት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወደኋላ እንደመለሰው የጠቆመው ይህ ዓለም ዐቀፍ ድርጅት፤
እስከ ጎሮጎሳውያኑ 2025 ድረስ ኮሮና ቫይረስ 2.5 ሚሊዮን ሕጻናት ገና በለጋ እድሜያቸው እንዲዳሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲልም ስጋቱን አጋርቷል።
ወረርሽኙ ድህነት እየጨመረ፤ ሕጻናትን ከትምህርት ውጪ እያደረገ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለትዳር እያጋለጣቸው ነው ያለው ሴቭ ዘ ችልድረን፤ በደቡብ እስያ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ የሚገኙ ሴት ሕጻናት ደግሞ የበለጠ ተጋላጭ እንደሚሆኑም አስረድቷል።
መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው ድርጅት መንግሥታት ሴት ሕጻናት ያለ እድሜያቸው እንዳይዳሩ ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ከማቅረቡ ባሻገር፤ “መሰል ጋብቻዎችን የሴቶችን መብት የሚጥሱ፣ ለድብርት እና ጥቃት የሚያጋልጡ ከፍ ሲልም ለሞት የሚዳርጉ ናቸው” ብሏል።
በመላው ዓለም በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ሕጻናት ያለ እድሜያቸው እንደሚዳሩ የገለጸው የሕጻናት መብት ተሟጋቹ ድርጅት፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስን ተከትሎ ያለ እድሜያቸው የሚዳሩ ልጆች ቁጥር  ከዚህ እንደሚጨምር ከወዲሁ አስጠንቅቋል።
በጎሮጎሳውያኑ 2020 ላይ ብቻ 500 ሺኅ ሴት ልጆች ተገደው የተዳሩ ሲሆን ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴት ልጆች ደግሞ ለእርግዝና ያለጊዜያቸው እንደሚዳረጉ ተገምቷል።
በመሆኑም መንግሥታት እና ድርጅቶች አስፈላጊውን እርምጃ ካልወሰዱ፣ በ2025 ላይ ያለ እድሜያቸው የሚዳሩ ልጆች ቁጥር ከ61 ሚሊዮን በላይ ይሆናል ሲል ሴቭ ዘ ችልድረን የችግሩን አሳሳቢነት ጠቁሟል።

LEAVE A REPLY