ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በኮሮና ቫይረስ ተያዙ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በኮሮና ቫይረስ ተያዙ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተነገረ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቅርብ አማካሪያቸው በኮሮናቫይረስ መያዟን ተከትሎ እርሳቸው እና ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርገው ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ መናገራቸውን ተከትሎ፣ የምርመራ ውጤቱ እርሳቸው እና ባለቤታቸው በቫይረሱ መያዛቸውን ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።
በኮሮና ቫይስ ተይዘዋል የተባለው የትራምፕ አማካሪ የ31 ዓመቷ ሆፕ ሂክስ ናቸው። “እኔ እና ቀዳማዊት እመቤት በቫይረሱ ተይዘናል። እራሳችንን ለይቶ ወደ ማቆየት እና ወደማገገም ሂደት በፍጥነት እንጀምራለን” ሲሉም ትራምፕ ይፋ አድርገዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ የምርጫ ክርክር ለማድረግ ወደ ኦሃዮ ባቀኑበት ወቅት ሆፕ ሂክስ አብራቸው በኤር ፎርስ ዋን የተጓዘች ሲሆን፣ ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ መሪን ዋን በተሰኘው የፕሬዝዳንቱ ሄሊኮፍተር ውስጥ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በቅርበት ሆና መጓዟ እየተነገረ ነው።
የትራምፕ በቫይረሱ መያዝ ሁለተኛውን ፕሬዝዳንታዊ ክርክር እንዴት ሊያውክ እንደሚችል ግልጽ ባይሆንም፤ ሁለተኛው የፊት ለፊት ክርክር በፍሎሪዳ ማያሚ ውስጥ ጥቅምት 15 ለማካሄድ ፕሮግራም ተይዞለታል።
ኮሮና ቫይረስ በአሜሪካ  ከ7.2 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ያጠቃ ሲሆን፣ ከ200 ሺኅ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ደግሞ ምክንያት ሆኗል። የትራምፕና ባለቤታቸው በቫይረሱ መያዙን ተከትሎ ዋይት ሃውስ ለሁሉም የፕሬዝዳንቱ አማካሪዎች እና ከፕሬዝዳንቱ ጋር በየዕለቱ ለሚገናኙ ሰዎች በሙሉ ምርመራ እንደሚያደርጉ መመሪያ እንደሚሰጥም ገልጿል።

LEAVE A REPLY