ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው የእነ ጃዋር መሐመድ ጠበቆች ጫናና ማስፈራሪያ ከተለያዩ አካላት እየደረሰብን ነው ሲሉ አስታወቁ።
ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ከተከሰተው ኹከት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉትን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ አባላት እንዲሁም ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች እየተከታተሉ የሚገኙትና 13 አባላት ያሉት የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ተወካይ የሆኑት አቶ ምስጋን ሙለታ ናቸው ቅሬታቸውን ለቢቢሲ ያቀረቡት።
ከጠበቆቹ መካከል በተወሰኑት ላይ በተለያዩ ጊዜያት እየገጠማቸው ያለው ጫናና ማስፈራሪያ እየበረታ መምጣቱን የሚናገሩት የሕግ ባለሙያዎቹ፤ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ በእጅጉ እያሳሰባቸው እንደሆነም ገልጸዋል።
የጠበቆቹ ቡድን ተወካይ እየደረሰብን ነው ያሉትን ችግር በተመለከተ አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጠቃላይ ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ፀጋ ቅሬታውን አጣጥለውታል።
ጠበቆቹ እየደረሰብን ነው ያሉትን ተጽዕኖ አስመልክቶ እስካሁን ድረስ ለጽሕፈት ቤታቸው የደረሰ ምንም ዓይነት መረጃ የለም ያሉት አቶ ፍቃዱ ፀጋ፤ “የተባለውን ነገር በተመለከተ መረጃ የለኝም። እነርሱ የሕግ ባለሙያዎች ናቸው፤ የሕግ ባለሙያ ስለሆኑ እንዲህ አይነት ችግር ሲገጥማቸው ለየትኛው አካላት ማሳወቅ እንዳለባቸው ያውቃሉ። እስከ አሁን በዚህ ረገድ አንድም የደረሰን ቅሬታ የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በሌሎቹ ተከሳሾች ጉዳይ ላይ በቡድን በመሆን ፍርድ ቤት በመቅረብ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት ጠበቆች፤ በሙያችን ለደንበኞቻችን ቆመን በመከራከራችን ምክንያት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚደርስብን ማስፈራሪያ እና ችግር እየበረታ መጥቷል በማለት መንግሥትን እየተቹ ነው።
“አንድ ቀን በቡራዩ ከተማ ፍርድ ቤት ለአንድ ተከሳሽ ተከራክሬ ስወጣ በፖሊስ ተጠራሁ። ከዚያም ወደ ቢሮ እንደገባሁ ያስጠራኝ ሰው ዘለፋና ተገቢ ያልሆኑ ቃላትን በመጠቀም ስልኬን ተቀብለው መፈተሽ ጀመሩ። ሸኔ ነህ ብለውም አስረው አጉላልተውኛል” በማለት ገጠመኛቸውን በምሳሌነት ያቀረቡት ጠበቃ ምስጋን፤ በአዲስ አበባ ከተማ የአራዳ ፖሊስ ጣቢያ የተገኙት ሌላ የጠበቆቹ ቡድን አባል የሆኑት አንድ የሕግ ባለሙያ ላይ በጦር መሳሪያ ማስፈራራት እንደተፈጸመባቸውም አስረድተዋል።