በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ አምስት ዞኖችና አንድ ወረዳ በጋራ ክልል ለመሆን ያቀረቡት...

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ አምስት ዞኖችና አንድ ወረዳ በጋራ ክልል ለመሆን ያቀረቡት ጥያቄ በም/ቤቱ ፀደቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በጋራ አንድ ክልል ለመመስረት ያቀረቡት ጥያቄ በሙሉ ድምፅ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ፀደቀላቸው።

5ኛው የፌደሬሽን ምክር ቤት 6ኛ አመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባዔ በዛሬው እለት ሲካሄድ በክልል የመደራጀቱን ጥያቄ ያቀረቡት  የካፋ፣ ቤንች-ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ዳውሮ፣ ሸካ ዞኖችና የኮንታ ልዩ ወረዳ መሆናቸው ታውቋል።
 ምክር ቤቱ በቀረበው ጥያቄ ላይ ሠፋ ያለ ውይይት ካደረገ በኋላ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።
እነዚህ ሕዝቦች ተቀራራቢ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ታሪክና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ስላለን አንድ ላይ ብንሆን የተሻለ ነው በማለት ጥያቄያቸውን ማቅረባቸው በምክር ቤቱ ውይይት ላይ ተገልጿል።
የክልልነት ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች በአጠቃላይ 13 መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ተለይተው የቀረቡት ዞኖች የተቀመጠውን መስፈርቶች አሟልተው የተገኙ እንደሆኑና በቀጣይም መሰፈርቶችን አሟልተው ለሚመጡ ዞኖች ጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚያገኝ በዛሬው መደበኛ ጉባዔ ላይ መወሰኑ ተሰምቷል።
ምክር ቤቱ በተጨማሪም ከህገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የቀረቡ የህገ መንግሥት ትርጉም የውኔሳ ሀሳቦች፣ የህገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በሚል ውሳኔ በተሰጣቸው እና ለምክር ቤቱ በይግባኝ በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ  የተወያየ ሲሆን፤ በህገ መንግሥት ትርጉም እና ማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረቡ የውሳኔ ሀሳቦችን ተመልክቶ በሙሉ ድምፅ እንዳፀደቃቸው ለማወቅ ተችሏል።

LEAVE A REPLY