የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ጋር

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ጋር

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛው ዙር የፓርላማ ዘመን 6ኛ አመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡

መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛው ዙር የፓርላማ ዘመን 6ኛ አመት አንደኛ መደበኛ ጉባዔ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ከውሳኔዎቹ መካከልም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ የከፋ፣ የቤንች ሸኮ፣ የዳውሮ፣ የሸካ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ም/ቤቶች ያቀረቡትን የጋራ ክልል ምሰረታ ጥያቄ ተቀብሎ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈፃሚነት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው ከሕገ መንግስት ትርጉም ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሲሆን በሕገ መንግስት ትርጉምና ማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረቡ የውሳኔ ሀሳቦችን ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡ በተጨማሪም ምክር ቤቱ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያግዙ ታምኖ የቀረቡትን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ረቂቅ አዋጅ እና የግብርና ምርት ውል ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት በሕ/ተ/ም/ቤት ሕግ ሆኖ እንዲወጡ ይሁንታ ሰጥቷል፡፡

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በ3ቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የ2013 በጀት አመት እቅዶች ላይ ሲሆን እቅዶቹ በሕገ መንግስቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተሰጡ ስልጣንና ተግባራት፣ ምክር ቤቱ ከጀመረው ሪፎርም እና ካለፈው የቋሚ ኮታ የአፈፃፀም ስኬቶችና ውስንነቶች አንፃር ተቃኝተው የቀረቡ መሆናቸውን ተቀብሎና እቅዶቹን የሚያዳብሩ ሀሳቦችን አክሎ የቀረቡትን እቅዶች አፅደቋል፡፡ በተያያዘም የቋሚ ኮሚቴ እቅዶች የ2012 በእቅድ የተያዙ ሥራዎችና ውሳኔዎች አፈፃፀም ግምገማን በመነሻነት የያዙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተለይም የ2012 ዓ.ም የምክር ቤቱ የሕገ መንግስት ትርጉም ውሳኔዎች አፈፃፀም ክትትል በተመለከተ አጽእኖት ተሰጥቶት ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ከተካሄደው ኢ-ሕገ መንግስታዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በክልሉ መንግስት የወጡ ህጎች፣ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተፈፀሙ ተግባራት ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይፀኑ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ናቸው በማለት የሕገ መንግሥት ትርጉም መስጠቱን በማስታወስ ይህንኑ ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ የውሳኔውን አፈፃፀም ሲከታተል መቆየቱንና ባደረገው ክትትልም ውሳኔው አለመፈፀሙን ማረጋገጥ እንደቻለ ለምክር ቤቱ አቅርቧል፡፡ አያይዞም ቋሚ ኮሚቴው የሚከተሉትን የውሳኔ ሀሳቦች አቅርቦ በምክር ቤቱ ፀድቀዋል፡፡

የትግራይ ክልል ያካሄደውን ኢ-ሕገ መንግስታዊ ምርጫ ተከትሎ ከተመሰረቱት የትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካል ጋር የፌዴራል መንግስት ምንም አይነት ግንኙነት ማድረግ የማይችል መሆኑ፣
የፌዴራል መንግስት የትግራይ ሕዝብን የሰላም፣ የልማት እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ፍላጎት ማዕከል በማድረግ የወረዳ፣ የከተማ እና የቀበሌ አስተዳደሮችን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ህጋዊ ተቋማት ጋር ብቻ የሥራ ግንኙነት ማድረግ እንዳለበት፣

የዚህን ውሳኔ አፈፃፀም የተከበሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና ጉዳዩ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በቅርበት መከታተል አለባቸው በማለት ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

(የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት)

መሰከረም 26/01/2013ዓ.ም
አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY