ሁለተኛው አውሮፕላን ዛሬ በምስራቅ ሐረርጌ ጃርሶ ወረዳ መውደቁ ተነገረ

ሁለተኛው አውሮፕላን ዛሬ በምስራቅ ሐረርጌ ጃርሶ ወረዳ መውደቁ ተነገረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጃርሶ ወረዳ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የኬሚካል ርጭት ሲያከናውን የነበረ አነስተኛ አውሮፕላን መውደቁ ተሰማ።

ዛሬ ሐሙስ የጃርሶ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብዱል ቃድር ደዚ ፤ አውሮፕላኗ ዛሬ ከቀኑ ስድስት ሰዐት አካባቢ “ጊደያ በሃ”  ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ኬሚካል ለመርጨት በቅኝት ላይ የነበረ አነስተኛ አውሮፕላን መውደቁን አረጋግጠዋል።
የአንበጣ ወረርሽኙ በቀበሌዋ ከተከሰተ አራተኛ ቀኑን ሲሆን፣ አንበጣው በጣም ከመብዛቱ የተነሳ በአራት ቀበሌዎች በሚገኝ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተከትሎ የኬሚካል ርጭት  ለማከናወን አውሮፕላኑ ወደ ስፍራው በመምጣት እየዞረ እያለ ነበር ድንገተኛ አደጋ የደረሰበት።
በዛሬው ዕለት በምሥራቅ ሐረርጌ ጃርሶ ወረዳ ጊደያ በሃ ቀበሌ በደረሰው አደጋ በአውሮፕላኑ ውስጥ አብራሪው ብቻ የነበረ ቢሆንም ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰበትም ታውቋል።
“አብራሪው አልተጎዳም፤ በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ወደ ድሬዳዋ የተወሰደው፤ አውሮፕላኑ ጎማው ላይ ብቻ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን ቀሪው የአካል ክፍሉ ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም” ያሉት አስተዳዳሪው አብራሪውም በሌላ አውሮፕላን ለሕክምና ወደ ድሬደዋ መወሰዱን ገልጸዋል።
የአንበጣ መንጋው በጃርሶ ወረዳ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ውስጥ በማሽላ እና በቆሎ የመሳሰሉ የሰብል አይነቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ እየተነገረ ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፈው ሳምንት መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ወረባቦ ወረዳ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል በመርጨት ላይ የነበረ አውሮፕላን ፍራንጉል በሚባል ቦታ ወድቆ መከስከሱ አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY