ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካል የሚረጩ 5 ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ከውጪ ለማስገባት ጥረት እያደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ለመከላከል ተግባሩ ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ የተከሰተው የበርሀ አንበጣ መንጋ ከተጠበቀውና ከቅድመ ማስጠንቀቂያው ግምቶች በላይ በመሆኑ በሰብሎች ላይ ያልተጠበቀ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተከሰተው የበረሀ አንበጣ መንጋ 5ኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኝና በቀን ከ50 እስከ 100 ኪሎ ሜትር መብረር የሚችል በመሆኑ ይህን በተገቢው መቆጣጠር ካልተቻለ የጉዳት መጠኑ ሊጨምር እንደሚችል ነው የተገመተው።
ጉዳቱን ለመከላከል የአውሮፕላን ርጭት አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ አሁን ካሉት አምስት አውሮፕላኖች በተጨማሪ 5 አውሮፕላኖችን ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የበርሀ አንበጣው በባህሪው ንፋስን ተከትሎ የሚስፋፋ በመሆኑ ከወዲሁ ክልሎች የሰው ኃይል በማስተባባር የጀመሩትን የመመከላከል ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
የበርሃ አምበጣ ክስተትን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ በማድረግ በአርሶ አደሩ ጉዳት የፖለቲካ ትርፍ አስልተው የሚንቀሳቀሱ አካላት የሚያሰራጩት መረጃ የመከላካል ጥረቱን እየጎዳው ነውም ተብሏል።
አርሶ አደሩን ለድንጋጤና ለተስፋ መቁረጥ የሚዳርጉ ተግባራት ችግርን የሚያባብሱ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ያልተጠና እና ያልተጣራ መረጃ ከማሰራጨት በመቆጠብ በመከላካል ጥረቱ በጎ አስተዋፅዖ እንዲያደርግ የግብርና ሚኒስትሩ መልእክት አስተላልፈዋል።