ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር አወዛጋቢው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ” ተከብቤያለሁ” ሲል ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በተፈጠረ ኹከት የሰው ህይወት ያጠፉ ተከሳሾች በእስራት መቀጣታቸው ተሰማ።
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቦረዳ ከተማ በህግ ጥላ ሥር የነበሩ ግለሰብ ላይ አሰቃቂ ግድያ የፈጸሙ ሁለት ተከሳሾች፣ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገልጿል።
ቅጣቱ የተላለፈው በነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱት መገርሳ ያሲን እና አረቢ ሻዶ በተባሉ ግለሰቦች ላይ መሆኑን የፍርድ ቤቱ ዳኛ አሸናፊ ሼዱ ይፋ አድርገዋል።
ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጃዋር መሃመድ ተከብቤያለሁ በሚል ካስተላለፈው ጥሪ ጋር ተያይዞ ሰልፍ በመውጣት በከተማው በተፈጠረው ኹከትና ግርግር ላደረሱት የነፍስ ማጥፋት ወንጀልና ንብረት ማውደም ውሳኔው መተላለፉም ተነግሯል።
ሁለቱ ተከሳሽ ግለሰቦች በህግ ጥላ ሥር የነበሩ አንድ ግለሰብን በአስገዳጅ ሁኔታ በሃይል በመውሰድ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለመግደላቸው በዐቃቤ ህግ ማስረጃዎች መረጋገጡንም የጠቆሙት ዳኛው፤ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን የዐቃቤ ህግ ምስክር ሊከላከሉ ባለመቻላቸውና ወንጀለኛነታቸውም በመረጋገጡ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል ብለዋል።
ዳኛው ይህን ይበሉ እንጂ ከእስረኛው ሟች በተጨማሪ በሐረር የተለያዮ ሥፍራዎች “የጃዋር መንጋ” በአማራ ተወላጆችና በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ እጅግ ዘግናኝ የሚባል ጭፍጨፋ ማከናወናቸውና በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።
በተለያዮ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቁ ጥቃቱን የሚያሳዮ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና በቂ የሰው ምስክሮች ቢኖሩም በሐረር ለተገደሉ ንጹሃን ዜጎች ትክክለኛ ፍርድ በሌሎች ላይ አለመሰጠቱ በሀገሪቱ ያለውን የሕግ አፈጻጸም ጥያቄ ያስነሳበታል ተብሏል።
በተመሳሳይ በአርሲ፣ በባሌ፣ በአምቦ፣ በሻሸመኔና በተለያዮ የኦሮሚያ ዞኖች በወቅቱ የጃዋር መሐመድ ደጋፊዎች በግፍ ጨፍጭፈው ለገደሏቸው ከ90 በላይ ለሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች ወንጀለኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሳይወሰድ ከቀረ ድፍን አንድ አመት ሊሞላው ሀያ ቀናት ብቻ ቀርተዋል።