ኢትዮጵያ ነገ ዜና || እሁድ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ. ም ባሌ ሮቤ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ በነበሩ ወጣቶች ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ አንድ ወጣት ተገድሏል መባሉን ተከትሎ ምርመራ ተጀመረ።
የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ እና የተለያዮ የዐይን እማኞች ወጣቱ መገደሉን ቢያረጋግጡም፤ ክስተቱ ሰልፍ ሳይሆን በከተማው ረብሻ ለመፍጠር የተደረገ ሙከራ እንደነበርም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሰልፉ ላይ ከተሳተፉትና ስሙን መግለፅ ያልፈለገ ወጣት ከጠዋቱ 3 ሰዐት እስከ 4 ሰዐት ገደማ ከ15-20 የሚጠጉ ወጣቶች በሮቤ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂዱ እንደነበር ጠቁሞ፤ “ሰልፉ ላይ ጀዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ ይፈቱ የሚልና በኦሮሚያ ግድያ መቆም አለበት የሚሉ መፈክሮቸን እያሰማን ነበር” ሲልም የነበረውን ሁኔታ አስታውሷል።
“ሰላማዊ ሰልፉ ከተጀመረ ከ30 ደቂቃ በኋላ ግሪን ካፌ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከኋላ መጥቶ ከበበን። ከዚያም ተኩስ ከፈቱብን። ሰልፉን በተኑ። ልጁ የተገደለው ያኔ ነው። ይሄን ልጅ መግደላቸው ሕብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣና ሀዘን ፈጥሯል” በማለት ወጣቱ በፖሊሶች መገደሉን አረጋግጧል።
ወጣቱ በተገደለበት ወቅት እሱም ግራ እጁን በጥይት መመታቱን የተናገረ ሌላ ወጣት ደግሞ፤ “በቦታው ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ ወጣቶች እንደነበሩ ፖሊሶች ከኋላችን መምጣታቸውን አየን። ከአውራሪስ ሰፈር ተነስተን፣ በአረጎው መናኸርያ ጋር አልፈን ግሪን ካፌ ጋ ደረስን። እዛ ስንደርስ ነው ፖሊሶቹ ከኋላችን መምጣታቸውን ያየነው” ብሏል።
“ፖሊሶቹ ተኩስ ሲጀምሩ መሮጥ ጀመርን። እኔም ሮጬ ዘልዬ የሆነ ሱቅ ውስጥ ገባሁ። ግራ እጄን፣ ከክንዴ በላይ በጥይት መመታቴን የተረዳሁት ያኔ ነው” ሲልም እሁድ እለት የተፈጠረውን አስታውሷል።
የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ አንድ ወጣት መገደሉን አምነው፤ ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ይገኛል ሲሉ ተደምጠዋል። “ሁኔታውን ሰልፍ ብሎ ለመጥራት ያስቸግራል። ምክንያቱም ቁጥራቸው ከ10 እስከ 15 ቢሆን ነው። ረብሻ ለመፍጠር ሙከራ እንዳደረጉ ነው የምንረዳው። እነዚህ ወጣቶች ተደራጅተው ድምጽ እያሰሙ ለረብሻ ቅስቀሳ እያደረጉ ነበር። በወቅቱ የጸጥታ ኃይል በቦታው ስለነበር ቶሎ ማስቆም ችሏል” ሲሉም የወጣቶቹን ድርጊት ኮንነዋል።